የዩኤኢ መከላከያ ከሀውሲ አማጺያን ለሶስተኛ ጊዜ የተተኮሰበትን ሚሳኤል አከሸፈ
የየመኑ የሀውሲ አማጺያን ወደ ዩኤኢ ለሶስተኛ ጊዜ ባሊስቲክ ሚሳኤል ተኩሰዋል
ጥቃቱ የተፈጸመው የእስራኤሉ ፕሬዝዳንት ዩኤኢን በመጎብኘት ላይ እያሉ ነው
የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች (ዩ.ኤ.ኢ) መከላከያ ከሀውሲ አማጺያን ለሶስተኛ ጊዜ የተተኮሰበትን ሚሳኤል አከሸፈ።
ሀውሲ የተሰኙት የየመን አማጺያን ዛሬ ሌሊት ወደ ዩኤኢ ባሊስቲክ ሚሳኤል ቢተኩሱም አደጋ ሳያደርሱ በሀገሪቱ መከላከያ ሃይል በዓየር ላይ እያሉ እንዲመክኑ መደረጋቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
አማጺያኑ እስካሁን ሶስተኛ ጊዜ ከተኮሱት ባሊስቲክ ሚሳኤሎች ውስጥ ሁለት ጊዜ የተተኮሱት አደጋ ሳያደርሱ እንዲመክኑ የተደረገ ሲሆን፤ በመጀመሪያዎቹ የሚሳኤል ጥቃቶች ሶስት ሰዎች ሲሞቱ ስድስት ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል።
የአሁኑ የባሊስቲክ ሚሳኤል ጥቃቅ የእስራኤሉ ፕሬዝዳንት ይስሃቅ ሄርዞግ የተባበሩት አረብ ኢምሬትን በመጎብኘት ላይ እያሉ የተፈጸመ ነው።
የባሊስቲክ ሚሳኤል ጥቃቱ የእስራኤሉ ፕሬዘዳንት የዩኤኢ ጉብኝታቸውን አቋርጠው እንዲመለሱ ለማድረግ ቢሆንም ፕሬዝዳንቱ ጉብኝታቸውን እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።
አሜሪካ ዩኤኢ ባለፉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ ሶስት ጊዜ በሀውሲ አማጺያን ባሊስቲክ ሚሰሳኤሎች መተኮሳቸውን ገልጻ ድርጊቱን አውግዛለች።
በአቡዳቢ የሚገኙት የእስራኤሉ ፕሬዝዳንት በዛሬው ውሏቸው የዱባይ 2020 ኤክስፖን እንደሚጎበኙ ይጠበቃል።
የዩኤኢ ሲቪል አቪዬሽን እንዳስታወቀው የሀገሪቱ የአየር ትራፊክ ምንም አይነት የደህንነት ስጋት እንደሌለበት እና በረራዎች በተያዘላቸው ጊዜያት ይቀጥላሉም ተብሏል።
የሀውሲ አማጺያን ባሳለፍነው ሳምንት ያደረሱትን ጥቃት ተከትሎ በርካታ ሀገራት ያወገዙ ሲሆን፤ ኢትዮጵያም ጥቃቱን አውግዛ ድርጊቱ የአካባቢውን ሀገራት ሰላም ያናጋል ማለቷ ይታወሳል።