ከ10 ሺህ በላይ አትሌቶች የሚፎካከሩበት የፓሪስ ኦሎምፒክ በዛሬው እለት ይጀመራል
የአረብ ኤምሬትስ የኦሎምፒክ ኮሚቴ በፈረንሳይ ፓሪስ በዛሬው እለት በሚጀመረው ኦሎምፒክ የሚሳተፉ አትሌቶችን ዝርዝር ይፋ አድርጓል።
ኤምሬትስ በ33ኛው ኦሎምፒክ በ14 አትሌቶች ትወከላለች። አትሌቲክስ፣ ብስክሌት፣ የውሃ ዋና፣ ጁዶ እና የፈረስ ግልቢያ ደግሞ የሚወዳደሩባቸው የስፖርት ዘርፎች ናቸው።
ከስታዲየም ውጭ ለመጀመሪያ ጊዜ በሚደረገው የኦሎምፒክ መክፈቻ ኦማር አል ማርዙቂ የኤምሬትስን ሰንደቅ ይዞ ከፊት ይመራል ተብሏል።
ሳፊያ አል ሳየህ በኦሎምፒክ ኤምሬትስን ወክሎ በመወዳደር ቀዳሚው ሆኗል።
መርያም ሞሀመድ አል ፋርሲ ደግሞ በሴቶች 100 ሜትር ውድድር ትሳተፋለች።
24 የህክምና፣ የቴክኒክና አስተዳደር ባለሙያዎችም ከአትሌቶቹ ጋር ወደ ፓሪስ አቅንተዋል።
ኤምሬትስ በ2004ቱ የአቴንስ ኦሎምፒክ እና በ2016ቱ የሪዮ ዴጄኔሮ ኦሎምፒክ በጂዶ ስፖርት የወርቅ እና የነሃስ ሜዳልያዎችን ማግኘቷ ይታወሳል።
ከስአታት በኋላ የሚጀመረው የፓሪስ ኦሎምፒክ መክፈቻ ስነስርአት እየተጠበቀ ነው።
በመላ ፈረንሳይ የባቡር ትራንፖርት መቋረጥ ከወዲሁ መክፈቻውን እንዳያደበዝዘው ስጋት ቢፈጥርም የኤምሬትስን ጨምሮ 206 ሀገራትን የወከሉ አትሌቶች በጀልባዎች የሚያደርጉት ደማቅ ጉዞ ይጠበቃል።
ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በፓሪስ ምልክት ኤፍል ታወር 33ኛው ኦሎምፒክ በይፋ መከፈቱን ያበስራሉ።