የአረብ ኢሚሬትስ ፕሬዝዳንት “ዓለማችን ውስብስብ ፈተናዎች እየተጋፈጠች ነው” አሉ
ፕሬዝዳንቱ ፤ኢሚሬትስ በ2050 የግሪንሀውስ ጋዝ ልቀትን የመቀነስ ራዕይዋን እውን ለመድረግ ቢሊዮን ዶላሮች ፈሰስ እያደረገች ነው ብለዋል
አረብ ኢሚሬትስ የፓሪስ የአየር ንብረት ስምምነትን ተቀብለው ከፈረሙ የቀጣናው ሃገራት መካከል ቀዳሚዋ ነች
የአረብ ኢሚሬትስ ፕሬዝዳንት ሼክ ሞሃመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን ዓለማችን ውስብስብ ፈተናዎች እየተጋፈጠች ነው አሉ።
ፕሬዝዳንቱ በግብጽ ሻርም አል ሼክ ከተማ እየተካሄደ ባለውና በርካታ የዓለም መሪዎች በተገኙበት 27ኛው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ (ኮፕ-27) ላይ ባደረጉት ንግግር ከፈተናዎቹ ዋነኛው “የአየር ንብረት ለውጥ” ነው ሲሉ ተናግረዋል።
“ዛሬ የተገናኘነው ለምድራችን ወሳኝ በሆነ ወቅት ላይ ነው፤ ዓለማችን የአየር ንብረት ለውጥን ጨምሮ ውስብስብ ፈተናዎች እየተጋፈጠች ነው ይህም በዓለም ላይ መረጋጋትን እና ደህንነትን እየጎዳ ነው” ብለዋል ሼክ ሞሃመድ ቢን ዛይድ።
ሼክ ሞሃመድ ቢን ዛይድ ንግግራቸው ሲቀጥሉም ፤ ያለን አንድ መሬት ብቻ ስለሆነ በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ለሚወሰደው ርምጃ ጥረታችንን አንድ ማድረግ አስፈላጊ ነው ብለዋል።
የአረብ ኢሚሬትስ ኃላፊነት ከሚሰማቸው የኃይል አቅራቢዎች መካከል እንደመሆኗ ለዓለም የሚሆን አነስተኛ ካርበን ያለው ነዳጅ እና ጋዝ በማቅረብ ረገድ የምትጫወተው ሚና እንደምትቀጥልበትን የኢሚሬትስ መስራች አባት ሼክ ዛይድ በጀመሩት አካሄድ መሰረት በዘርፉ ያለውን ልቀትን በመቀነስ ላይ ትኩረት እድርጋ እየሰራች መሆኑም ነው የተናገሩት ፕሬዝዳንቱ።
“ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ እድገትን ለማነቃቃት ኢኮኖሚያችንን በማብዛት እና የታዳሽ ሃይል አቅማችንን በማሳደግ ላይ ነን” ሲሉም አክለዋል።
የአረብ ኢሚሬትስ በ2050 የግሪንሀውስ ጋዝ ልቀትን ለመቀነስ ያላትን ራዕይ ይፋ ያደረገችና ወደ ተግባር የገባች የመጀመሪያዋ ሀገር ነች ያሉት ፕሬዝዳንት ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ አል፤ የተቀመጠውን ራዕይ እውን ለማድረግ ከቀናት በፊት ከአሜሪካ ጋር 100 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስት ስምምነት መፈራረሟ አንስተዋል፡።
ስምምነቱ በተለያዩ የዓለም ሀገራት 100 ጊጋዋት ንጹህ ኢነርጂ ለማመንጨት የሚያስችል መሆኑም ተናግረዋል።
“አረብ ኢሚሬትስ ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጋር የትብብር እና የግንኙነት ድልድዮችን የመገንባቱን አካሄድ ትቀጥላለች” ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።
በፈረንጆቹ 2023 የሚካሄደውን 28ኛውን የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ በምናዘጋጅበት ወቅት በባለፉት ጉባዔዎች የተላለፉ ውሳኔውችን መሰረት በማድረግ ተፈጻሚነታቸው ላይ እናተኩራለን ሲሉም አክለዋል።
ሼክ ሞሃመድ ቢን ዛይድ፤ በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ውጤት ለማምጣት በሚደረገው ጥረት መላውን ዓለም በማሳተፍ ዘላቂ መፍትሄዎችን ተግባራዊ እናደርጋለን ያሉ ሲሆን ኪሳራዎችን እና ጉዳቶችን ለመቅረፍ እንዲሁም የእድገት እድሎችን ለመፍጠር አስተዋጽዖ የሚያደርጉ ተግባራዊ መፍትሄዎችን ለማግኘት ሁሉም እንዲተባበርም ጥሪ አቅርበዋል።
የአየር ንብረት ለውጥ ከባድ ተጽዕኖን ሊያሳርፍ ቢችልም የስራ ዕድል ሊፈጠርበት እንደሚችል ይታመናል።
የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ ለኢነርጂ ዘርፍ አማራጮች ትኩረት መስጠቷንና በዘርፉ ብዙ ሀብት ፈሰስ ማድረጓን የዚህ ሁነኛ ማሳያ ነው።
አረብ ኢሚሬትስ የዓለም አቃፍ ታዳሽ ኃይል ዓመታዊ ጉባዔ ቋሚ አዘጋጅና የፓሪስ የአየር ንብረት ስምምነትን ተቀብለው ከፈረሙ የቀጣናው ሃገራት መካከልም ቀዳሚዋ ነች።
ግዙፍ የጸሃይ ኃይል አማራጮችን ከገነቡና በርካሽ ከሚያቀርቡ ሀገራት መካከልም ናት።
ለታዳሽ ኃይል ግንባታዎች ትኩረት ሰጥታ የምትሰራው ኢምሬትስ በ6 አህጉራት በሚገነቡ የታዳሽ ኃይል ልማት ፕሮጄክቶች ላይ 17 ቢሊየን ዶላር ገደማ ገንዘብን ፈሰስ ማድርጓ እንዲሁም በተለያዩ አጋሮቿ በኩል በድጋፍና ብድር መልክ 1 ቢሊየን ዶላር ፈሰስ ማድረጓንም መረጃዎች ያመለክታሉ።