የሀገራቱ ግንኙነት የአረብ ሃገራትን ትብብር የማጠናከሩ አንድ አካል ነው ተብሏል
አረብ ኢምሬት እና ኳታር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን አደሱ።
ላለፉት ዓመታት ተቋርጦ የነበረው የተባበሩት አረብ ኢምሬት እና ኳታር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዲቀጥል ስምምነት ላይ ተደርሷል።
እንደ አረብ ኢምሬት ዜና አገልግሎት (ዋም) ዘገባ ከሆነ ሁለቱ ሀገራት በአል-ኡላ ስምምነት መሰረት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸው እንዲቀጥል ወስነዋል።
በዚህ ስምምነት መሰረትም ኳታር በአረብ ኢምሬት አቡዳቢ ኢምባሲዋን እንዲሁም በዱባይ ደግሞ ቆንሱላ ጽህፈት ቤቷን ትከፍታለች።
የተባበሩት አረብ ኢምሬት ደግሞ በኳታር መዲና ዶሀ ኢምባሲዋን እንደምትከፍት ተገልጿል።
የሁለቱ ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መታደስ የአረብ ሀገራት ትብብር አካል ነው ተብሏል።
አረብ ኢምሬት ከዚህ በፊት ከኢራን እና ቱርክ ጋር የነበራትን የሻከረ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን ማደሷ ይታወሳል።
ከኢራን ጋር ለብዙ ዓመታት የሻከረ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የነበራት ሌላኛዋ ሀገር ሳውዲ አረቢያ በቻይና አሸማጋይነት ግንኙነቷን ማደሷ አይዘነጋም።
ከአረብ ሊግ ታግዳ የነበረችው ሶሪያ ከ12 ዓመታት መገለል በኋላ ወደ መድረኩ የተመለሰች ሲሆን ፕሬዝዳንት በሽር አላሳድ ከአንድ ወር በፊት በሪያድ በተካሄደው የአረብ ሊግ ጉባኤ ላይ ተሳትፈዋል።