አረብ ኢሚሬትስ በውጭ ንግድ በዓመቱ መጀመሪያዎቹ ዘጠኝ ወራት የ19 በመቶ እድገት ማስመዝገቧ ገለጸች
አረብ ኢሚሬትስ ከመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት መካከል ቀዳሚዋ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ሀገር ናት
አረብ ኢሚሬትስ በ2022 መጨረሻ የውጭ ንግድ መጠኗን 2.2 ትሪሊየን ድርሃም ለማድረስ እየሰራች ነው
አረብ ኢሚሬትስ በውጭ ንግድ በዓመቱ መጀመሪያዎቹ ዘጠኝ ወራት የ19 በመቶ እድገት ማስመዝገቧ ገለጸች
የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ ምክትል ፕሬዝዳንትና ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሁም የዱባይ ገዥ ሼክ መሀመድ ቢን ራሺድ አል ማክቱም ሀገራቸው በውጭ ንግድ በ2022 የመጀመሪያዎቹ ዘጠኝ ወራት የ19 በመቶ እድገት ማስመዝገቧን ገልጸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ሼክ መሀመድ ቢን ራሺድ አል ማክቱም በትዊተር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት "የዓለም ንግድ ድርጅት የዓለም ንግድ እድገት መጠን ወደ 3.5 በመቶ ለማድረስ እጅግ ከባድ እንደሚሆን ቢተነብይም፤ የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ በመጀመሪያዎቹ ዘጠኝ ወራት ውስጥ የ19 በመቶ እድገት በማስመዝገብ የተለየ ሁኔታ ፈጥራለች፤ በዚህም ባለፈው አመት ከነበረው የ1.9 ትሪሊየን ድርሃም የንግድ መጠን ሲነጸጸር በ2022 መጨረሻ የውጭ ንግድ መጠናችን 2.2 ትሪሊየን ድርሃም ይደርሳል ብለን እንጠብቃለን” ብለዋል፡፡
አክለውም “የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ በዓለም አቀፍ ንግድ እና ኢኮኖሚ ልዩ የሆነች ሀገር ነች… እና በአገልግሎት እና በመሰረተ ልማት ረገድ የተለየች ናት…የተረጋጋ ዓለምአቀፍ ግንኙነት ያላት ሀገር ናት.. ፈጣሪ ቢፈቅድ የበለጠ ጠንካራና ከፍ ያለ ስኬት የሚመዘገብበት አመት እንደሚሆን ተስፋ አለን…ፈጣሪ ኢሚሬትስን እና ህዝቦቿን ይጠብቅ" ሲሉም አክለዋል የተባበሩት አረብ ኢሚቴትስ ምክትል ፕሬዝዳንትና ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሁም የዱባይ ገዥ ሼክ መሀመድ ቢን ራሺድ አል ማክቱም፡፡
አረብ ኢሚሬትስ ከመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት መካከል ቀዳሚዋ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ሀገር እንደሆነች የዓለም አቀፉ የሀገራት ዓመታዊ ኢንቨስትመንት ሪፖርት ያመለክታል፡፡
እንደዚህ ተቋም ሪፖርት ከሆነ ኢሚሬትስ ከዓለማችን ሀገራት መካከል ዘጠነኛዋ የኢንቨስትመንት ሳቢ ሀገር ሆና ተመርጣለች፡፡
የዓለም ኢኮኖሚ በኮሮና ቫይረስ ክፉኛ በተመታበት የ2021 ዓመት እንኳን 20 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት እንደሳበች ሪፖርቱ ይገልጻል፡፡
ኢሚሬትስ በዓለማችን ካሉ ሰፊ መንገደኞችን ማስተናገድ የሚችሉ ቀልጣፋ የአውሮፓላን ጣቢያዎች ካሏቸው ሀገራት መካከል ተጠቃሽ ሀገር ስትሆን ኢምሬት አየር መንገድ እና ኢትሃድ አየር መንገድ ዋነኞቹ ናቸው፡፡
ባለፉት 10 ዓመታት ውስጥ በኢምሬትስ ገንዘባቸውን ያፈሰሱ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ቁጥር በ52 በመቶ ጭማሪ እንዳሳየም ይነገራል፡፡
በአጠቃላይ በኢሚሬትስ 2 ሺህ 577 ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች በተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ የተሳተፉ ሲሆን የ114 ሀገራት ዜግነት ያላቸው ሰዎችም በሀገሪቱ በተለያዩ ስራዎች ላይ ተሰማርተው ይኖራሉ፡፡