ዩኤኢ 200 ሜትሪክ ቶን የምግብ እርዳታዎችን ነው ወደ ትግራይ የላከችው
የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች (ዩኤኢ) ከዓለም የምግብ ፕሮግራም ጋር በመተባበር ለትግራይ ክልል የሚሆኑ የምግብ እርዳታዎችን የጫነ አውሮፕላን ላከች፡፡
እርዳታዎቹን የጫነው አውሮፕላን ከዩኤኢ ለትግራይ ክልል የተላኩ ሰብዓዊ ድጋፎችን የጫነ የመጀመሪያው አውሮፕላን ሲሆን ድጋፉን በሚያስተባብሩ የኤመራት የሰብዓዊ ቡድን አባላት ታጅቧል፡፡
ዩኤኢ 200 ሜትሪክ ቶን የምግብ እርዳታዎችን ነው ወደ ትግራይ የላከችው፡፡
ይህ የትኛውም ሰብዓዊ ችግር በገጠመ ጊዜ ዩኤኢ ከኢትዮጵያ እና ከዓለም ህዝብ ጎን እንደምትቆም የሚያሳይ ነው ተብሏል፡፡
በኢትዮጵያ የዩኤኢ አምባሳደር መሃመድ ሳሊም አህመድ ሙሳድ አል ረሺድ እንደተናገሩት ዩኤኢ በትግራይ ሰብዓዊ ድጋፎችን ለማድረግ እና የምግብ እርዳታዎችን ለማቅረብ ፍላጎት አላት፡፡
አሁን የተላከው እርዳታም ዩኤኢ ለድጋፍ በተፈለገችበት ቦታ ሁሉ ለመገኘት ላላት ቆርጠኝነት ማሳያ ነው እንደ አምባሳደሩ ገለጻ፡፡
ዩኤኢ ከአሁን ቀደምም ለኢትዮጵያ የተለያዩ የኮሮና ክትባቶችን ድጋፍ አድርጋለች፡፡
የዓለም የምግብ ፕሮግራም የምስራቅ አፍሪካ አስተባባሪ ሚሼል ዳንፎርድ በበኩሉ ወቅቱን ለጠበቀው እርዳታ ዩኤኢን አመስግኖ ድጋፉን በቶሎ ትግራይ ለማድረስ እንደሚሰሩ አስታውቋል፡፡
የዩኤኢ የውጭ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስቴር ከአሁን ቀደም ኤመራት ከኢትዮጵያ እና ከህዝቦቿ ጎን እንደምትቆም በመጠቆም ግጭቱ እንዲረግብና በውይይት እንዲፈታ ደግማ ጥሪ ማቅረቧ የሚታወስ ነው፡፡
የዓለም ሰብዓዊ ቀን ነገ በዓለም አቀፍ ደረጃ ይከበራል፡፡
ይህን አስመልክተው መልዕክት ያስተላለፉት የዩኤኢ ምክትል ፕሬዝዳንት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የዱባይ ገዢ ሼክ መሃመድ ቢን ረሺድ አል መክቱም ሃገራቸው እስካሁን 320 ቢሊዬን ዲርሃም ለስብዓዊ ድጋፍ ማድረጓል አስታውቀዋል፡፡
በዩኤኢ ለሚገኙ በጎ አድራጊዎች የወርቅ ቪዛ መስጠት ጀምረናልም ነው ሼክ መሃመድ ያሉት፡፡