ምክር ቤቱ 47 ሃገራትን በአባልነት የያዘ ነው
የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች (ዩኤኢ) የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት አባል ሆነች፡፡
ዩኤኢ180 የድጋፍ ድምጾችን በማግኘት ነው ምክር ቤቱን ለቀጣዮቹ 3 ዓመታት በአባልነት የተቀላቀለችው፡፡
ከፈረንጆቹ 2022 እስከ 2024 በምክር ቤቱ የምታገለግልም ይሆናል፡፡
ሃገሪቱ የዚህ ምክር ቤት አባል የሆነችው ከ193 የዓለማችን አገራት የ180 አገራትን ድምጽ በማግኘት ነው።
ዩኤኢ ለዚህ ምክር ቤት አባል ተደርጋ የተመረጠችው በአገር ውስጥ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ በሰብዓዊ ልማት ዙሪያ በሰራችው ውጤታማ ስራ እንደሆነም ተገልጿል።
ዩኤኢ ከሰብዓዊ መብት ጋር በተያያዘ የአውሮፓ ፓርላማ ያሳለፈውን ውሳኔ ውድቅ አደረገች
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት 47 አባል አገራት ያሉት ሲሆን ውድድሩ በየ አህጉራት በመከፋፈል የሚከናወን ነው።
በዚህ መሰረት በእስያ አህጉር ስር የተባበሩት አረብ ኤምሬት፣ ኳታር፣ ህንድ፣ ማሌዢያ እና ካዛኪስታን የተመረጡ ሲሆን ከአፍሪካ ሶማሊያ፣ ካሜሩን፣ ቤኒን፣ ኤርትራ እና ጋምቢያ የምክር ቤቱ አባል ይሆናሉ ተብሏል።
በምስራቃዊ አውሮፓ ደግሞ ሞንቴኔግሮ እና ሉትዋኒያ የምክር ቤቱ አባል ለመሆን ሲያመለክቱ ፓራጓይ፣ ሆንዱራስ እና አርጀንቲና ደግሞ የደቡብ አሜሪካን ወክለው አባል እንደሚሆኑ ተገልጿል።
አሜሪካ፣ ፊንላንድ እና ሉግዘንበርግ ደግሞ የምዕራባዊያን አገራትን ወክለው በምክር ቤቱ ይሰየማሉ ተብሏል።
47 የዓለማችን አገራት በአባልነት በማቀፍ የሚንቀሳቀሰው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ምርጫ በሚስጥር የሚካሄድ ሲሆን ከፈረንጆቹ 2022 ጀምሮ ለሶስት ዓመታት ከቆየ በኋላ አዲስ ምርጫ ይካሄዳል።