በብሪታንያ ከአልኮል መጠጥ ጋር በተያያዘ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በሀገሪቱ ታሪክ ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱ ተገለጸ
በ2023 በሀገሪቱ ከአልኮል መጠጥ ጋር በተያያዘ ከ10 ሺህ በላይ ሰዎች ህይወታቸው አልፏል
ባለሙያዎች መንግስት የአልኮል ሽያጭ እና ማስታወቂያን የሚገድብ ፖሊሲ እንዲያዘጋጅ ጠይቀዋል
በብሪታንያ ከአልኮል መጠጥ ጋር በተያያዘ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በሀገሪቱ ታሪክ ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱ ተገለጸ፡፡
በአልኮል መጠጥ ሳቢያ የሞቱ ሰዎች ቁጥር በአራት ተከታታይ አመታት ውስጥ ከፍተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የሀገሪቱ የብሔራዊ ስታቲስቲክስ ቢሮ አስታውቋል።
ቢሮው ባወጣው ሪፖርት መሰረት በ2023 በብሪታንያ ከአልኮል ጋር በተያያዘ በሚፈጠሩ በሽታዎች 10 ሺህ 473 ሞት ተመዝግቧል ።
የሞት ምጣኔው በ2022 ከተመዘገበው በ4 በመቶ ብልጫ ሲኖረው ከ2019 አንጻር ደግሞ የ38 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።
በ2023 ከ100 ሺህ ወንዶች መካከል 21.9 በመቶ የሚሆኑት ሲሞቱ ከ100 ሺህ ሴቶች መካከል 10.3 በመቶ የሚሆኑት ህይወታቸው አልፏል፡፡
የሀገሪቱ የብሔራዊ ስታቲስቲክስ ቢሮ አክሎም ከ2020 ጀምሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ከ25 እስከ 59 ዓመት እድሜ ላይ የሚገኙ ሰዎች የሞት መጠን መቀነሱን፤ በአንጻሩ ከ20 እስከ 24 እና ከ60 በላይ የሆናቸው የሞት መጠን ከ2022 ጋር ተመሳሳይ መሆኑን ነው ያመለከተው፡፡
ስኮትላንድ እና ሰሜን አየርላንድ በዩናይትድ ኪንግደም ከፍተኛውን የሞት መጠን በመያዝ ሲቀጥሉ በ2023 የስኮትላንድ የሞት ምጣኔ በ22.6 በመቶ ላይ ይገኛል፡፡
የአልኮል ጤና ህብረት ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ሰር ኢያን ጊልሞር የአልኮል መጠጦች ዋጋ ርካሽ መሆን፣ በየአካባቢው በቀላሉ ሊገኙ መቻላቸው እና ከመጠን በላይ መጠጣትን መደበኛ የሚያደርግ የማስታወቂያ ብዛት የዚህ ጤና ቀውስ መንስኤዎች ናቸው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ሊቀመንበሩ ይህን ስር የሰደደ ችግር ለመቀረፍ መንግስት በፖሊሲ ደረጃ ተግባራዊ የሚደረጉ መመሪያ እና ህጎችን በመላው ብሪታንያ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚኖርበት አሳስበዋል፡፡
የአልኮል መጠጥ ዋጋዎችን ማሻሻል፣ የማስታወቂያዎችን መጠን የሚገድብ መመሪያ እና ደንቦችን ማጽደቅ፣ አስገዳጅ የጤና ማስጠንቀቂያዎችን መለጠፍ እና በአልኮል ጤና ህክምና አገልግሎቶች ላይ የተሻለ ገንዘብ መበጀት በመፍትሄነት ቀርበዋል፡፡