በእንግሊዝ የኑሮ ውድነቱን ተከትሎ የትምህር ቀናት ወደ ሶስት ቀናት ዝቅ ሊደረጉ ነው
የነዳጅ ዋጋ እና የመምህራን ደመወዝ መጨመር ለትምህርት ቀናቱ መቀነስ ዋነኛ ምክንያቶች ሆነዋል
የእንግሊዝ ትምህርት ቤቶች በጉዳዩ ዙሪያ ለመወሰን በምክክር ላይ መሆናቸው ተገልጿል
በእንግሊዝ የኑሮ ውድነቱን ተከትሎ ትምህር ቀናት ወደ ሶስት ቀናት ዝቅ ሊደረጉ እንደሚችሉ ተገለጸ፡፡
ሩሲያ እና ዩክሬን ወደ ጦርነት ማቅናታቸውን ተከትሎ የዓለም ነዳጅና ምግብ ዋጋ እያሻቀበ ይገኛል፡፡ 40 በመቶ የአውሮፓ ሀገራትን ነዳጅ የምትሸፍነው ሩሲያ ጦርነቱ የአቅርቦት እና የዋጋ መዛነፍን አስከትሏል፡፡
ይሄንን ተከትሎም በአውሮፓ የምርቶች ዋጋ ያሻቀበ ሲሆን ሰራተኞች የደመወዝ ማስተካከያዎች እንዲደረግላቸው በተለያዩ መንገዶች በመጠየቅ ላይ ይገኛሉ፡፡
በእንግሊዝ ያሉ ትምህርት ቤቶች የነዳጅ ዋጋ መጨመር እና የኑሮ ውድነቱን ተከትሎ መምህራን ደመወዝ እንዲጨመርላቸው ጫና ማሳደር መጀመራቸውን ተከትሎ ትምህርት ቤቶች የህልውና አደጋ አደጋ እንደተደቀነባቸው ዘ ቴሌግራፍ ዘግቧል፡፡
ይሄንንም ተከትሎ በሳምንት አምስት ቀናት ይሰጥ የነበረው የትምህርት ስርዓት ወደ ሶስት ቀናት ለማድረግ በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ዘገባው አክሏል፡፡
በተለይም የመምህራን ደመወዝ ከሚቀጥለው መስከረም ወር ጀምሮ ጭማሪ እንደሚደረግበት መገለጹን ተከትሎ እና ቀጣዮቹ ቀዝቃዛ ወራትን ታሳቢ በማድረግ ትምህርት ቤቶች ወቺያቸው እንደሚጨምር ይጠበቃል፡፡
ይህ የወጪ መጨመር ያሳሰባቸው የሀገሪቱ ትምህርት ቤቶች በሳመንንት አምስት ቀናት የነበረውን የተማሪዎች ማስተማር ሰርዓትን ወደ ሶስት ቀናት ዝቅ የማድረግ እቅድ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡
በመላው እንግሊዝ ያሉ የትምህርት ቤቶቹ ሃላፊዎችም በጉዳዩ ዙሪያ ወጥ የሖነ አቋም እና ውሳኔ ለማስተላለፍ ምክክር መጀመራቸውንም ዘገባው አክሏል፡፡
ይሁንና የእንግሊዝ መንግስት እስከ ፈረንጆቹ 2024 ድረስ ለትምህርት ቤቶቹ ድጎማ ሰባት ቢሊዮን ዩሮ እንደሚደጉም ቢያሳውቅም ውሳኔው በቂ አይደለም ሲሉ ትምህርት ቤቶች ውድቅ አድርገዋል፡፡
ትምህርት ቤቶቹ የመንግስትን ድጎማ በጀት እንደማይቀበሉት የገለጹት መንግስት በአንድ ተማሪ ያስቀመጠው የድጎማ ተመን እና አሁን ያለው የኑሮ ውድነት የማይመጣጠን ነው በሚል ነው፡፡