አሜሪካ እና ሶማሊያ ሽብርተኝነት ለመዋጋት የሚያደርጉት ትብብር አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገለጹ
በሶማሊያ ፖለቲከኛች መካከል የነበረው ሽኩቻ “አልሻባብ እንዲያንሰራራ” እድል የፈጠረ መሆኑ ይነገራል

የሶማሊው ፕሬዝዳንት ፤ “አሜሪካ በሶማሊያ ዘላቂ ልማት እና እድገት ውስጥ ስትራቴጂካዊ አጋር ነች” ብለዋል
አሜሪካ እና ሶማሊያ ሽብርተኝነት ለመዋጋት የሚያደርጉት ትብብር አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገለጹ፡፡
ለይፋዊ ስራ ጉብኝት በአሜሪካ የሚገኙት የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ ከአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ጋር ተገናኝተው በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡
ሽብርተኝነትን መዋጋት፣ የሶማሊያ ድረቅ እና መልካም አስተዳደር ፕሬዝዳንቱ ከአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር በነበራቸው ቆይታ የመከሩባቸው አንኳር ጉዳዮች ናቸው፡፡
በውይይታቸው በተለይም ከሶማሊያ አልፎ የቀጠናው ስጋት የሆነውን ሽብርተኝነት ለመዋጋት ሀገራቱ የሚያደርጉት ትብብር አጠናክረው ለመቀጠል መስማማታቸው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ በትዊተር ገጻቸው ያጋሩት መረጃ ያመለክታል፡፡
“አሜሪካ በሶማሊያ ዘላቂ ልማት እና እድገት ውስጥ ስትራቴጂካዊ አጋር ነች”ም ብለዋል ፕሬዝዳንቱ፡፡
አሁን አሁን ከነበረበት ሁኔታ እያንሰራራ እየመጣ እንደሆነ የሚነገርለት አልሻባብን አደጋ ለመግታት በሚል፤ አሜሪካ በታጣቂ ቡድኑ ላይ የተለያዩ እርምጃዎች በመውሰድ ላይ መሆኗ የሚታወቅ ነው፡፡
በተጨማሪም ፕሬዝዳንት ባይደን የቀጠናው ስጋት የሆነውን አልሻባብ ለመምታት 600 የሚሆኑ የሃገራቸውን ወታደሮች ወደ ሶማሊያ እንደሚልኩ ማስታወቃቸው የሚታወስ ነው።
የአሜሪካ ጦር በድጋሚ በሶማሊያ እንዲሰማራ የማድረግ ውሳኔ በየሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ ተቀባይነት ማግኘቱም አይዘነጋም፡፡
ሶማሊያ አሁንም በአልሻባብ እየተፈተነች ነው። በተለይም ከምርጫ ጋር በተያያዘ በሃገሪቱ ፖሊተከኞች መካከል የነበረው ሽኩቻ ለሰላምና ጸጥታ ይሰጥ የነበረውን ትኩረት አላልቶት እንደነበር በርካቶች ያነሳሉ።
አሁኑ ላይ አሜሪካ በአልሻባብ ላይ የምትወስዳቸው እርምጃዎች አሜሪካ ቡድኑን ከማዳከም አንጻር ትልቅ ሚና እንደሚጫወት ይታመናል፡፡
የአሜሪካን ሚና እንደ ትልቅ የአጋርነት መገለጫ አድረጎ የሚወስደው የፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ አስተዳደር በቅረቡ "ለመረጋጋትና ሽብርተኝነትን ለመዋጋት በምናደርገው ትግል አሜሪካ ወትሮም ቢሆን ታማኝ አጋራችን ናት" ሲል በትዊተር ገጹ ላይ ባወጣው ጽሁፍ ማጋራቱም የሚታወስ ነው፡፡