ተሸናፊው የወግ አጥባቂ ፓርቲ በታሪኩ አነሰተኛውን የምክርቤት ወንበር እንደሚያገኝ ተገምቷል
በብሪታንያ ትናንት በተካሄደው ጠቅላላ ምርጫ የሌበር ፓርቲ አብላጫውን መቀመጫ ማግኘቱ ተነገረ።
ፓርቲው እስካሁን ባለው ግምት ከአጠቃላይ 650 የምክር ቤት ወንበር 380 ማሸነፉን የቢቢሲ ግምት ያሳያል።
የወግ አጥባቂው ፓርቲ በበኩሉ 144 ወንበር እንደሚያገኝ የተገለጸ ሲሆን፥ ይህም በታሪኩ አነስተኛው ነው ተብሏል።
የሌበር ፓርቲው መሪ ኪር ስታመር ፓርቲያቸው በምርጫው በማሸነፉ ለደጋፊዎቻቸው የደስታ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የምርጫው ውጤት በይፋ ተገልጾ የጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ ተተኪ ይሆናሉ ተብለው የሚጠበቁት ስታመር፥ በኑሮ ውድነት፣ መሰረታዊ የህዝብ አገልግሎት እጦትና ሌሎች ፈተናዎች የተጋረጠውን “ቀውስ” ለመፍታት ዛሬውኑ ስራ እንጀምራለን ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ ፓርቲያቸው ለገጠመው ሽንፈት ሃላፊነት እንደሚወስዱ የገለጹ ሲሆን፥ ለአሸናፊው ኪር ስታመር ስልክ ደውለው መልካም ምኞታቸውን ገልጸውላቸዋል።
በትናንቱ ምርጫ የሪፎርም ብሪታንያ ፓርቲ መሪው ኒጀል ፋራጅ ከስምንተኛ ሙከራ በኋላ ፓርላማ መግባታቸውን የሚያረጋግጥ ድምጽ ማግኘት ችለዋል።
ሌበር ፓርቲ በምርጫው አብላጫውን በማግኘት ቢያሸንፍም የህዝቡን አመኔታ ለማግኘት ፈጣን የለውጥ እርምጃዎችን መውሰድ ይጠበቅበታል ነው የተባለው።
በተለይ የግብር ጫናን የመቀነስና የዜጎችን የኑሮ ሁኔታ ማሻሻል እንዲሁም ብሄራዊ የጤና አገልግሎትን ዳግም ስራ ማስጀመር ከኪር ስታመር የዳውኒንግ ስትሪት ቆይታ ከሚጠበቁ ጉዳዮች ዋናዋናዎቹ ናቸው።
ስታመር የወግ አጥባቂው ፓርቲ ማስፈጸም የጀመረውን ወደ ብሪታንያ በህገወጥ መንገድ የገቡ ጥገኝነት ጠያቂዎችን ወደ ሩዋንዳ የመላክ ፖሊሲ እሰርዛለሁ ሲሉ ቃል መግባታቸውን ሬውተርስ አስታውሷል።
የሌበር ፓርቲ መሪው በአነስተኛ ጀልባዎች ከፈረንሳይ ወደ ብሪታንያ የሚገቡ በአስር ሺዎች የሚቆጥሩ ሰዎች ለመቆጣጠር ጠንካራ የመፍትሄ ሃሳብ እንዲያስቀምጡ ጫና ይደረግባቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።
ከ14 አመታት በኋላ ወግ አጥባቂውን ፓርቲ የሚተካው ሌበር ፓርቲ መሪው ኪር ስታመር ዛሬ ከሪሺ ሱናክ ጋር የስልጣን ርክክብ እንደሚያደርጉ እየተጠበቀ ነው።
ከስልጣን ርክክቡ አስቀድሞ ግን የብሪታንያው ንጉስ ቻርለስ ሶስተኛ ስታመር አዲስ መንግስት እንዲያዋቅሩ በይፋ ይጠይቋቸዋል ተብሏል።