ብሪታንያ ዜጎቿ የውጭ ሀገር ዜጎችን እንዳያገቡ የሚገድብ ህግ አወጣች
የውጭ ሀገር ዜጋ የሚያገቡ ዜጎች 45 ሺህ ዩሮ ዓመታዊ ገቢ ሊኖራቸው ይገባል ተብሏል
ሀገሪቱ አዲስ ህግ ያወጣችው የውጭ ሀገር ዜጎችን የሚያገቡ ብሪታንያዊያን በመጨመራቸው ነው
ብሪታንያ ዜጎቿ የውጭ ሀገር ዜጎችን እንዳያገቡ የሚገድብ ህግ አወጣች።
አውሮፓዊቷ ሀገር የስደተኞችን ቁጥር ለመቀነስ ያለመ ህግ ማውጣቷን አስታውቃለች።
አዲሱ ህግ የሌላ ሀገር ዜግነት ያላቸው ብሪታንያዊያንን ያስቆጣ ሲሆን ህጉ እንዲታገድ አልያም ማሻሻያ እንዲደረግበት እንቅስቃሴ ጀምረዋል ተብሏል።
እንደ ቢቢሲ ዘገባ አዲሱ ህግ ፍቅረኞቻቸው ወይም ባሎቻቸውን ከተለያዩ ሀገራት ወደ ብሪታንያ ማምጣት የሚፈልጉ ዜጎች የግድ የተሻለ ገቢ ሊኖራቸው እንደሚገባ ይደነግጋል።
አንድ የብሪታንያ ዜጋ የሌላ ሀገር ዜጋ ለማግባት ዓመታዊ ገቢው የግድ 45 ሺህ ዩሮ መሆኑን ማረጋገጥ ይኖርበታል ተብሏል።
አስተያየቷን ለቢቢሲ የሰጠች አንድ ብሪታንያዊት "ከእንግዲህ የውጭ ዜጎችን ማግባት የሚችሉት ሀብታሞች ብቻ ናቸው ይህ በጣም ያሳዝናል" ብላለች።
ከዚህ በፊት በስደተኝነት ቪዛ ያገኙ የብሪታንያ ዜግነት የሌላቸው ሰዎች ቪዛቸውን ለማራዘም የግድ በአዲሱ ህግ መሰረት የተቀመጡ ቅድመ ሁኔታዎችን ማሟላት አለባቸው መባሉን ተከትሎ በርካታ ሰዎች ከሀገሪቱ ሊባረሩ እንደሚችሉም ተገልጿል።
ብሪታንያ ይህን ህግ ያወጣችው በጋብቻ ሰበብ ወደ ግዛቷ የሚገቡ የውጭ ሀገር ዜጎች እየጨመረ በመምጣቱ እንደሆነ አስታውቃለች።
በባህር እና በሌሎች መንገዶች ወደ ብሪታንያ የሚገቡ ስደተኞን ወደ አፍሪካዊቷ ሩዋንዳ በግድ መመለስ የሚያስችል ህግ አጽድቃ እንደነበር ይታወሳል።
የሀገሪቱ ፍርድ ቤት ይህን ህግ እንዳይፈጸም ያገደ ቢሆንም ከዚህ ህግ ጋር ተቀራራቢ የሆነ አዲስ ህግ መዘጋጀቱ ነው የተገለጸው።