ብሪታንያ 22 ጠቅላይ ሚኒስትሮችን ስትቀያየር የተመለከቱት የ104 አመት መንትዮች
አንደኛው የአለም ጦርነት ከተጠናቀቀ በኋላ የተወለዱት መንትዮች አሁንም ደስተኛ ህይወት እንደሚመሩ ይናገራሉ
ረጅም እድሜ የመቆየታችን ሚስጢርም መንታ መሆናቸው ያጎናጸፋቸው ልዩ መተሳሰብና ፍቅር መሆኑን ይገልጻሉ
የብሪያንያ የረጅም እድሜ ባለጠጎቹ መንትያ እህትማማቾች 104ኛ አመት ልደታቸውን በጋራ አክብረዋል።
አንደኛው የአለም ጦርነት በተጠናቀቀ በአመቱ በአንድ ስአት ልዩነት ይህቺን ምድር የተቀላቀሉት ኢማ እና ቴልማ ሃሪስ ከማንቸስተር በ11 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ጥንታዊ ከተማ ስቶክፖርት ነው የተወለዱት።
እህትማማቾቹ የመጀመሪያው የአለም ጦርነትን በእናታቸው ማህጸን ቢያሳልፉም 19ኛ አመታቸውን ሲይዙ ሁለተኛውን ለመመልከት ተገደዋል።
ብሪታንያ ሶስት ንጉሳዊ ስርአቶችን ስትለውጥና 22 ጠቅላይ ሚኒስትሮች ዳውኒንግ ስትሪት ገብተው ሲወጡም ተመልክተዋል።
በ14 አመታቸው ከትምህርታቸው ጎን የእቃ ማሸግ ስራ ሲጀምሩ፤ በ21 አመታቸው በሶስት ወራት ልዩነት ትዳር ሲመሰርቱም ሆነ በአጠቃላይ ኑሯቸው መመሳሰል የሚወዱት መንትዮች 104 አመት ሆኗቸውም በላንክሻየር በአንድ ቤት ውስጥ ነው የሚኖሩት።
“አንድ ክፍለዘመን ሙሉ እንደምርጥ ጓደኛ ነው የኖርነው፤ በወጣትነታችን ድብድብና ንትርክ ቢኖርም እየጎለመስን ስንሄድ መተሳሰቡ እያየለ ሄዷል” ብለዋል ኢማ ሃሪስ ከሚረር ጋር በነበራቸው ቆይታ።
መንታ መሆናችሁ ምን አስገኘላችሁ ለሚለው ጥያቄም፥ “ሌላ ጓደኛ ሳያስፈልገን እርስ በርስ እንድንተሳሰብ እና እንድንዋደድ አድርጎናል” ባይ ናቸው።
ሁለተኛው የአለም ጦርነት የትዳር አጋሮቻቸውን ያሳጣቸው መንትዮቹ ምሽት ላይ ሎሚ የተጨመረበት ውሃ አልያም ብራንዲ የመጎንጨት የዘወትር ልምዳቸውም “ወደ ወጣትነት ስሜት” እንደሚመልሳቸው ይገልጻሉ።
“የወጣትነት ስሜት ከተሰማህ ረጅም ጊዜ ሳታረጅ ትዘልቃለህ” የሚሉት ቴልማ፥ እንደ ወጣት አዳዲስ ልብሶችን ለመግዛትና አዳዲስ ነገሮችን ለመመልከት የመውጣት ልምድ እንዳላቸው ተናግረዋል።
“104 አመት አመት የመቆየታችን ሚስጢር ቀላል ነው፤ እንደወጣት ማሰብ፣ መተሳሰብና ሁሌም ምሽታችን ተናፋቂና ደስተኛ ማድረጋችን ነው” ሲሉም ያክላሉ።