የብሪታኒያ መከላከያ ሚኒስቴር አደጋው እንዴት እንደተከሰተ እየመረመርኩ ነው ብሏል
ሁለት የብሪታኒያ የጦር መርከቦች በባህሬን ወደብ ላይ እርስ በእርስ መጋጨታቸው ተገለፀ።
በማህበራዊ ሚዲያ ላይ በሰፊው የተሰራጨው ቪዲዮ ኤችኤምኤስ ቺዲንግፎልድ የተባለ የጦር መርከብ ወደ ኤችኤምኤስ ባንጎር በማቅናት ሲጋጭ ያሳያል።
በግጭቱ ማንም የተጎዳ የለም ያለው የብሪታኒያ የመከላከያ ሚኒስቴር፤ “አደጋው እንዴት እንደተከሰተ እየመረመርኩ ነው፤ ምርመራው በቀጠለበት ወቅት ስለ ግጭቱ አስተያየት መስጠት አልችልም” ሲል ተቆጥቧል።
ሁለቱ የጦር መርከቦች የዩናይትድ ኪንግደም በባህረ ሰላጤው ውስጥ የረጅም ጊዜ ቆይታ አካል ናቸው።
የተጋጩት የጦር መርከቦች በውሃ ላይ ደህንነቱ የተጠበቀ የንግድ እንቅስቃሴ እንዲኖር የሚሰሩ መሆናቸውን የብሪታኒያ ሮያል የባህር ኃይል ተናግሯል።