ፖለቲካ
ዩክሬን የሩሲያ ጦር በባክሙት ግንባር 'ስኬት እያገኘ' ነው አለች
የዩክሬን ተዋጊዎች ለበርካታ ወራት የፈጀውን ጦርነት አሁንም የቀጠሉ መሆናቸውንም ሀገሪቱ አስታውቃለች
አንድ ዓመት በተሻገረው የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት ባክሙትና ዶኔትስክ ክልል የጥቃት ማዕከል ሆነዋል
የሩሲያ ጦር በምስራቅ ግንባር በባክሙት ከተማ "የተወሰነ ስኬት" ማግኘቱን የዩክሬን ወታደራዊ ባለስልጣናት ገልጸዋል።
የዩክሬን ተዋጊዎች ለበርካታ ወራት የፈጀውን ጦርነት አሁንም የቀጠሉ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
ለ13 ወራት በዘለቀው ጦርነት ሩሲያ በአጎራባች ዩክሬን ግዛቶች ለከፈተችው ጦርነት በአብዛኛው የማዕድን ከተማዋ ባክሙት እና የኢንዱስትሪ ክልሉ ዶኔትስክ የጥቃት ማዕከል ሆነዋል።
ሮይተርስ እንደዘገበው ሁለቱም ወገኖች በአካባቢዎቹ ሙሉ ቁጥጥር የሌላቸው ሲሆን፤ ሁለቱም ከባድ ኪሳራ ደርሶባቸዋል።
የዩክሬን ጦር ኃይሎች ጄኔራል "የጠላት ኃይሎች ባክሙትን ከተማ ለመውረር ያደረጉት እርምጃ በተወሰነ ደረጃ የተሳካ ነበር" ብለዋል።
"የእኛ ወታደሮች ከተማዋን በመያዝ በርካታ የጠላት ጥቃቶችን በመመከት ላይ ይገኛሉ" ሲሉም አክለዋል።
የሩሲያ ባለስልጣናትም በባክሙት ውስጥ በሚደረግ ውጊያ ኃይሎቻቸው መሬት እየያዙ ነው ብለዋል።