ፖለቲካ
ዩክሬን የተመድ ጸጥታው ምክር ቤት በሩሲያ የኒውክሌር እቅድ ላይ እንዲሰበሰብ ጠየቀች
ፕሬዝዳንት ፑቲን እርምጃው የኒውክሌር ቅነሳ ቃል ኪዳኖችን አይጥስም ብለዋል
ሞስኮና ሚንስክ ጠንካራ ወታደራዊ ግንኙነት አላቸው
ዩክሬን እሁድ እለት የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን "ታክቲካል የኒውክሌር ጦር መሳሪያን" በቤላሩስ ለማቋቋም የያዙትን እቅድ ክፉኛ ተችታለች።
እርምጃውን ለመግታትም የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባ እንዲያደረግ ጥሪ አቅርባለች።
ውሳኔውን ያሳወቁት ፑቲን እርምጃው የኒውክሌር ቅነሳ ቃል ኪዳኖችን እንደማይጥስ እና ሩሲያ የጦር መሳሪያ ለቤላሩስ አሳልፋ እንደማትሰጥ ገልጸዋል።
የዩክሬን ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ባወጣው መግለጫ ውሳኔውን የሞስኮ “ሌላ ቀስቃሽ እርምጃ” በማለት ገልጾታል።
“የዓለም አቀፍ የደህንነት ስርዓትን በአጠቃላይ” የሚጎዳ ነው በማለትም አክሏል።
የጸጥታው ምክር ቤት ስብሰባ እንዲያካሄድ የጠየቀ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴሩ፤ በተጨማሪም የቡድን ሰባት ሀገራት እና የአውሮፓ ህብረት ቤላሩስ መሳሪያ እንዳትቀበል እንዲያስጠነቅቅ ጠይቋል።
የቤላሩስ ጦር በዩክሬን ባለው ጦርነት በይፋ አልተዋጋም። ነገር ግን ሀገሪቱ ባለፈው ዓመት ለጦርነቱ ሞስኮ የቤላሩስን ግዛት እንድትጠቀም ፈቅዳለች ተብላል።
ሁለቱ ሀገራት የቅርብ ወታደራዊ ግንኙነት እንዳለቸው ሮይተርስ ዘግቧል።