የሩሲያና ዩክሬን ተወካዮች ሳይጨባበጡ ድርድራቸውን በኢስታንቡል ጀምረዋል
ዩክሬን ከሩሲያ ጋር በቱርክ ለመደራደር ኢስታንቡል የሚገኙ ተደራዳሪዎቿ እንዳይመረዙባት በመስጋት እንዲጾሙ አዛለች።
ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን ጦርን እቀላቀላለሁ ማለቷን ተከትሎ ሩሲያ ከዩክሬን ጋር ወደ ጦርነት ከገቡ ዛሬ 34ኛ ቀናቸውን ይዘዋል፡፡
ጦርነቱን ለማስቆም ሁለቱ ሀገራት በቤላሩስ ተገናኝተው ከሁለት ጊዜ በላይ የመከሩ ቢሆንም የሚታሰበውን ለውጥ ማምጣት አልተቻለም ነበር።
ከ20 ቀናት በፊትም የሁለቱ ሀገራት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢስታንቡል ተገናኝተው የመከሩ ቢሆንም የተገኘ ውጤት አልነበረም።
በዚህም ምክንያት ሩሲያ እና ዩክሬን የድርድር ቦታቸውን ወደ ቱርክ ኢስታንቡል ከተማ የቀየሩ ሲሆን በዛሬው ዕለትም የሁለቱ ሀገራት ተደራዳሪዎች ውይይታቸውን ማካሄድ ጀምረዋል።
ይሁንና ተደራዳሪዎቹ ሰላምታ ሳይለዋወጡ ወይም ሳይጨባበጡ ድርድራቸውን ጀምረዋል ተብሏል።
ዩክሬን በበኩሏ በኢስታንቡል የሚገኙት ተደራዳሪዎቿ እንዳይመረዙባት በመስጋት ምንም አይነት ምግብ እና ውሃ እንዳይመገቡ አስጠንቅቃለች።
ዩክሬን ተደራዳሪዎች በኢስታንቡል ቆይታቸው እንዲጾሙ ተጠይቀዋል።
የቱርኩ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶሃንም ለሁለቱ ሀገራት ተደራዳሪዎች አቀባበል ያደረጉላቸው ሲሆን ጦርነቱን አስቆሙት ሲሉ ለተደራዳሪዎቹ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዴሚር ዘለንስኪ ለሩሲያ ብዙሃን መገናኛዎች ጋር ባደረጉት ቃለመጠይቅ በኢስታንቡሉ ድርድር በሶስት ጉዳዮች ላይ ከሩሲያ ጋ ስምምነት ላይ መድረስ እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።
የደህንነት ዋስትና እና ኑክሌር አረርን አለመጠቀም ፕሬዘዳንቱ ከሩሲያ ጋር ስምምነት ላይ መድረስ የሚፈልጉባቸው ጉዳዮች እንደሆኑ ተገልጿል።
ይሀንና የኢስታንቡሉ ድርድር የሚያተኩረው ለንጹሃን ዜጎች ሰባዓዊ ድጋፍ ማድረግ ስለሚቻልባቸው እና በጦርነቱ እንዳይጎዱ ማድረግ ዋነኛ አጀንዳው እንደሆነ እየተገለጸ ይገኛል።
ከዚህ በተጨማሪም ዩክሬን ከሩሲያ ጋ ዘላቂ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲፈጸም እንደምትፈልግም አስቀድማ አስታውቃለች።
ከ34 ቀናት በፈፊት የተጀመረው የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት 4 ሚሊዮን ገደማ ዜጎች ወደ ጎረቤት ሀገራት የተሰደዱ ሲሆን ተጨማሪ ውድመት ሳይደርስ ጦርነቱ እንዲያበቃ በርካቶች በመወትወት ላይ ናቸው።