“ፑቲን በስልጣን መቆየት አይችልም” ማለታቸው በአሜሪካ ዘንድ የፖሊሲ ለውጥ መኖሩን እንደማያሳይ ባይደን ተናገሩ
በአሜሪካ በኩል በሩሲያ የአገዛዝ ለውጥ እንዲደረግ ፍላጎት እንደሌለም ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል
የተሰማኝን ነው የተናገርኩት ያሉት ባይደን ለንግግሩ የምጠይቀው ምንም አይነት ይቅርታ የለም ብለዋል
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ስልጣን ላይ መቆየት እንደማይችሉ መናገራቸው የግል አስተያየት እንጂ የሃገራቸው አቋም እንዳልሆነ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ተናገሩ፡፡
ባይደን ከንግግሩ ጋር በተያያዘ እንዲያብራሩ እና የፖሊሲ ለውጥ ስለመኖሩ እንዲናገሩ በጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
በምላሹ በአሜሪካ በኩል በሩሲያ የአገዛዝ ለውጥ እንዲደረግ ፍላጎት እንደሌለ ገልጸዋል፡፡
ንግግሩ ፑቲን በዩክሬን እያካሄዱ ካሉት ጦርነት ጋር በተያያዘ የሰጡት የግል አስተያየት እንጂ ፖሊሲን የተመለከተ ጉዳይ እንዳይደለም ነው የ76 ዓመቱ ባይደን የተናገሩት፡፡
"ያኔም አልነበረም አሁንም የፖሊሲ ለውጥ ስለመኖሩ እየገለጽኩ አይደለም። የተሰማኝን የሞራል ቁጣ ነው ስገልጽ የነበረው፤ እናም ምንም አይነት ይቅርታ አልጠይቅም" ሲሉም በኋይት ሀውስ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ አስቀምጠዋል፡፡
ባይደን ባሳለፍነው ቅዳሜ ወደ ፖላንድ አቅንተው በዋርሶው ጉብኝት አድርገው ነበር፡፡ በዚያም ተፈናቃይ ዩክሬናውያንን እና ሌሎች የጦርነቱ ሰለባዎችን ጎብኝተዋል፡፡ ከጉብኝቱ በኋላም ነበር ቭላድሚር ፑቲን ስልጣን ላይ ሊቆዩ እንደማይገባ የተናገሩት፡፡ ሆኖም በሁኔታው ውስጤ በመነካቱ የተናገርኩት ነው ብለዋል፡፡
ንግግሩ በተለይ በሩሲያውያን ዘንድ ቁጣን ፈጥሯል፡፡ የኋይት ሃውስ ባለስልጣናትም ንግግሩን ለማስተባበልና የአሜሪካ አቋም እንዳልሆነ ለማሳወቅ ሲጣደፉ ነበረ፡፡
ባይደን ከአሁን ቀደምም ፑቲን የጦር ወንጀለኛ እንደሆኑ መናገራቸው ይታወሳል፡፡ ይህን ተከትሎ ሩሲያ ይቅር አልለውም ስላለችው ስለዚሁ ንግግር ማብራሪያ ጠይቃ እንደነበርም አይዘነጋም፡፡