ዩክሬን ኤፍ-15 የተሰኘውን የጦር ጄት እንዲሰጧት በማሰባሰብ ላይ ትገኛለች
ዩክሬን የፈረንሳይ የጦር ጄቶችን እንደማትቀበል ገለጸች።
የዩክሬን እና ሩሲያ ጦርነት ከተጀመረ 18ኛ ወሩ ላይ የሚገኝ ሲሆን በየጊዜው አዳዲስ ክስተቶችን ማስተናገዱ እንደቀጠለ ነው።
ሩሲያ ጦርነቱን እንዳታሸንፍ የጦር መሳሪያ እና የገንዘብ ድጋፎችን በማድረግ ላይ ያለው የሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን ጦር ወይም ኔቶ ለዩክሬን ተጨማሪ ድጋፍ እንዲደረግ በማሳሰብ ላይ ነው።
የኔቶ አንድ አባል የሆነችው ፈረንሳይ ከአውሮፓ ሀገራት ከብሪታንያ እና ጀርመን ቀጥሎ ብዙ ድጋፎችን ያደረገች ሀገር ናት።
አሁን ደግሞ ሚራጅ የተሰኘውን የጦር ታንክ ለዩክሬን እሰጣለሁ ብትልም ዩክሬን ድጋፉን ውድቅ አድርጋለች።
ዩክሬን የፓሪስን ጥያቄ ውድቅ ያደረገችው ፈረንሳይ ልትሰጠው ያሰበችው የጦር ጀቶች ያረጁ ናቸው በሚል ነው ተብሏል።
የዩክሬን አየር ሀይል ቃል አቀባይ እንዳሉት ፈረንሳይ ለኪቭ ልትሰጠው ያሰበችው ሚራጅ የጦር ጀት ከሩሲያ ጋር ለሚደረገው ጦርነት አያግዝም በሚል ድጋፉን ውድቅ አድርጋለች።
ዩክሬን ኤፍ-15 የተሰኘውን የጦር ጄት ምዕራባዊያን ሀገራት እንዲለግሷት የጠየቀች ሲሆን ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ በብዙ ሀገራት እየተዟዟሩ ድጋፍ በማሰባሰብ ላይ ናቸው።
ለዩክሬን ከተለገሱ የጦር ታንኮች ውስጥ ግማሹ ለውጊያ ብቁ አይደሉም መባሉን ፎርብስ የኪቭ ባለስልጣናትን ጠቅሶ ዘግቧል።
ከተለያዩ ምዕራባዊያን ሀገራት ለዩክሬን የተለገሱ የጦር ታንኮች ከሀገሪቱ መልክዓምድር ጋር አመቺ ካለመሆኑ በተጨማሪ በሩሲያ ታንኮች በቀላሉ ለኢላማ እንደሚጋለጡም በዘገባው ላይ ተጠቅሷል።