ፕሬዝዳንት ዜለንስኪ ከሩሲያው አቻቸው ጋር “በቀጥታ ማውራት እፈልጋለሁ” ብለዋል
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜለንስኪ ከሩሲያው አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን ጋር በቀጥታ ለመነጋገር ጥያቄ ማቅረባቸውን አስታወቁ።
ዜለንስኪ በቀጥታ መነጋገር እንደሚፈልጉ ከመግለጽም ባለፈ ለፕሬዝዳንት ፑቲን “የፊት ለፊት ተገናኝተን እንነጋገር” ጥሪ አቅርበዋል።
ቁጭ ብለው ከፑቲን ጋር ማውራት እንደሚፈልጉ የገለጹት ፕሬዝዳንቱ ምዕራባውያን ወታደራዊ ድጋፋቸውን እንዲያጠናክሩም ጠይቀዋል።
በቢሯቸው ካለው ጠንከር ያለ ምሽግ ውስጥ መግለጫ የሰጡት ዜለንስኪ ሩሲያ አሁን ባለው ወታደራዊ መስፋፋቷ ከቀጠለች ሌሎች የአውሮፓ ሀገራትንም ልታጠቃ እንደምትችል ገልጸዋል።
“እኔ ፑቲንን ማውራት እፈልጋለሁ፤ ዓለም ፑቲንን ማውራት ይፈልጋል፤ ጦርነቱን ለማስቆም ሌላ አማራጭ የለም” ብለዋል ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜለንስኪ።
ዜለንስኪ፤ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲንን “ከእኛ ምንድነው የምትፈልጉት፣ መሬታችንን ለቃችሁ ወጡ” ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።
ፕሬዝዳንት ዜለንስኪ ፑቲንን “ቁጭ ብለው ከእኔ ጋር ይነጋገሩ፤ ግን በ30 ሜትር ርቀት መሆን የለበትም” ሲሉም ነው የተናገሩት።
ዜለንስኪ ይህንን የተናገሩት ቭላድሚር ፑቲን የዓለም መሪዎችን ሲያነጋግሩ በትልቅ ጠረንጴዛ መሆኑን በማንሳት ነው።
የዩክሬኑ መሪ ፑቲንን ለማናገር ላቀረቡት ጥያቄ ከክሬምሊን የተሰማ መልስ የለም። የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት የተጀመረው ባለፈው ሃሙስ ዕለት ነበር። ጦርነቱ በይፋ ባይቆምም እስካሁን የሞስኮ እና የኪቭ ፖለቲከኞች ሁለት ጊዜ ተነጋግረዋል።