ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ ዩክሬን መልሶ ማጥቃት ለመጀመር ዝግጁ ናት አሉ
ዩክሬን ለመልሶ ማጥቃቱ ከምዕራባዊያን የጦር መሳሪያ በመፈለግ ዲፕሎማሲያዊ ግፊት ላይ ናት
ኪየቭ ጦርነቱ ከተጀመረ ከ15 ወራት በኋላ ግዛቷን ለማስመለስ መልሶ ማጥቃትን ለመጀመር ተዘጋጅቻለሁ ብላለች
ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ ዩክሬን መልሶ ማጥቃት ለመጀመር ዝግጁ ናት አሉ።
ዩክሬን በሩሲያ የተያዘባትን ግዛት መልሶ ለመያዝ ለረጅም ጊዜ ሲጠበቅ የነበረው የመልሶ ማጥቃት ዘመቻ ለመጀመር ዝግጁ መሆኗን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ ተናግረዋል።
ዘለንስኪ ለዎል ስትሪት ጆርናል "እንደሚሳካልን አጥብቀን እናምናለን። ምን ያህል ጊዜ እንደሚወስድ አላውቅም። እውነቱን ለመናገር በተለያዩ መንገዶች ሊሄድ ይችላል። ፍጹም የተለየ ነው። ግን እኛ ልናደርገው ነው። እናም ዝግጁ ነን" በማለት ስለ መልሶ ማጥቃቱ ተናግረዋል።
ኪየቭ ጦርነቱ ከተጀመረ ከ15 ወራት በኋላ ግዛቷን ለማስመለስ አካሂደዋለሁ ያለችው አጻፋዊ ጥቃት የጦርነቱን ሚዛን እንደሚለውጥ ተስፋ አድርጋለች።
ዘለንስኪ ባለፈው ወር ዩክሬን የመልሶ ማጥቃት ከመጀመሯ በፊት ከምዕራባውያን ተጨማሪ የታጠቁ ተሽከርካሪዎች እስኪቀርቡ ድረስ መጠበቅ እንዳለባት ተናግረዋል።
የዩክሬን እቅድ ስኬታማ እንዲሆን ቁልፍ የሆነውን ተጨማሪ ወታደራዊ እርዳታ እና የጦር መሳሪያ በመፈለግ ፕሬዝዳንቱ የምዕራባውያንን ድጋፍ ለማስጠበቅ ዲፕሎማሲያዊ ግፊት ላይ ተጠምደው ቆይቷል።
ሩሲያ በምስራቅ፣ በደቡብ እና በደቡብ ምስራቅ የዩክሬን ግዛትን ይዛለች።
ላለፉት በርካታ ሳምንታት ዩክሬን በሩሲያ የጦር መሳሪያ መጋዘኖች እና የትጥቅ መስመሮች ላይ የምታደርገውን ጥቃት ጨምራለች ሲል ሮይተርስ ዘግቧል።
የዩክሬን ጦር በምስራቅ ዶኔትስክ ግዛት የምትገኘው ማሪይንካ የትግሉ ትኩረት እንደሆነች ተናግሯል።
የዩክሬን ኃይሎች በአካባቢው 14 የሩስያ ወታደሮች ጥቃትን ማክሸፋቸውን ጦሩ ተናግሯል።