የዩክሬኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በአፍሪካ ጉብኝት ሊያደርጉ ነው
የሚኒስትሩ ጉብኝት የአፍሪካ ሀገራት የዜለንስኪን የሰላም እቅድ እንዲደግፉ ማድረግ ያለመ ነው ተብሏል
የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች ሩሲያና ዩክሬን ለድርድር ዝግጁ ናቸው ማለታቸው ይታወሳል
የዩክሬኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲሚትሮ ኩሌባ በአፍሪካ ጉብኝት ሊያደርጉ መሆኑን አስታውቀዋል።
ሚኒስትሩ በዚህ ሳምንት የሚያደርጉትን ጉብኝት ከሞሮኮ እንደሚጀምሩ ነው የገለጹት።
የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ሁለተኛው ዙር ጉብኝታቸው ሩሲያ የአፍሪካ ሀገራት የዜለንስኪን የሰላም እቅድ እንዲደግፉ ለማድረግ ያለመ ስለመሆኑ ሬውተርስ ዘግቧል።
"ከአፍሪካ መሪዎች ጋር ወሳኝ ንግግሮች እያደረግን ነው” ያሉት ኩሌባ፥ በጥቁር ባህር በኩል የዩክሬን ስንዴ ለአፍሪካ ገበያ ያለመቆራረጥ እንዲቀርብ ከመሪዎቹ ጋር የሚደረገው ምክክር ትልቅ ፋይዳ እንዳለው አንስተዋል።
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ ባለፉት ቀናት በአረብ ሊግ እና የቡድን 7 አባል ሀገራት ጉባኤ ላይ የተገኙ ሲሆን፥ ከህንድ፣ ኢንዶኒዥያ፣ ኢራቅ እና ሳኡዲ አረቢያ መሪዎች ጋርም መክረዋል።
ፕሬዝዳንቱ ይፋ ያደረጉት ባለ 10 ነጥብ የሰላም እቅድም በሀገራቱ ይሁንታ እንዲቸረው ጠይቀዋል።
በሰላም እቅዳቸው ዙሪያም በነሃሴ ወር አለምአቀፍ ጉባኤ እንዲካሄድ ጥሪ ማቅረባቸው የሚታወስ ነው።
የሩሲያ ጦር ሙሉ በሙሉ ከዩክሬን የመውጣቱን ጉዳይ የማንደራደርበት ነው የሚለው የሰላም እቅድ በሞስኮ በኩል ተቀባይነት ያገኛል ተብሎ አይጠበቅም።
ከአፍሪካ ሀገራት ጋር ጠንካራ ግንኙነት የመሰረተችው ሩሲያ ላይ ጫና ለመፍጠርም ኬቭ ከፍተኛ ጥረት እያደረገች መሆኑ ተነግሯል።
በጥቅምት ወር በኪንያ፣ ጋና፣ ሴኔጋልና ኮቲድቯር ጉብኝት ያደረጉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯም፥ ለሁለተኛው ዙር እየተዘጋጁ ነው።
በዩክሬን ምድር ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ቻይናን ጨምሮ በርካታ ሀገራት ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ።
የሮማው ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀጳጳስ አባ ፍራንሲስም ሞስኮ እና ኬቭ ለመደራደር ዝግጁ መሆናቸውን መግለጻቸው አይዘነጋም።