የአቡዳቢ ልዑል አልጋ ወራሽ እና የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በዩክሬን ጦርነትና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ተወያዩ
ብሊንከን በእስራኤል የኔጌቭ ጉባዔ ላይ መሳተፋቸውም ይታወሳል
አንቶኒዮ ብሊንከን ከሰሞኑ በመካከለኛው መስራቅ ሃገራት ጉብኝት ላይ ናቸው
የአቡዳቢ ልዑል አልጋ ወራሽ እና የአረብ ኤሚሬቶች ጦር ኃይል ምክትል ጠቅላይ አዛዥ ሼክ መሃመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን ከአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒዮ ብሊንከን ጋር ተወያዩ፡፡
ልዑል አልጋ ወራሹ እና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በሞሮኮ ራባት ነው የተወያዩት፡፡
የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነትን ጨምሮ በየመን ስለሚንቀሳቀሱት የሃውሲ አማጽያን እንዲሁም በተለያዩ ቀጣናዊ የጸጥታና ደህንነት ጉዳዮች ላይ መወያየታቸውን የኤሚሬት ዜና አገልግሎት (ዋም) ዘግቧል፡፡
በውይይቱ የኤሚሬት የውጭ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ሼክ አብዱላህ ቢን ዛይድ አል ናህያንን ጨምሮ ሌሎች ባለስልጣናት ተገኝተዋል፡፡
ብሊንከን የሃገራቱን ትብብር የበለጠ ያጠነክራል ያሉትን ፍሬያማ ውይይት ከሼክ መሃመድ ጋር ማድጋቸውን በይፋዊ የማህበረሰብ ትስስር ገጻቸው አስታውቀዋል፡፡
ውይይቱን አስመልክቶ ማብራሪያ የሰጡት የብሊንከን ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስም ኤሚሬት የሃውሲ አማጽያን ከየመን ከሚፈጽሙባት ጥቃት ራሷን ለመከላከል የምታደርገውን ጥረት አሜሪካ በቁርጠኝነት እንደምትደግፍ ተናግረዋል፡፡
ኤሚሬት የየመን ችግር በዲፕሎማሲያዊ መንገዶች ብቻ ሰላማዊ መፍትሔዎችን ሊያገኝ ይገባል ማለቷንም አድንቀዋል፡፡
ብሊንከን እና ሼክ አብዱላህ ቢን ዛይድ ከሰሞኑ እስራኤል ነበሩ፡፡ ወደ ራባት ከማቅናታቸውም በፊት እስራኤል ከአራት የአረብ ሃገራት ጎረቤቶቿ ጋር ባዘጋጀችው የኔጌቭ ጉባዔ ላይ ተሳትፈዋል፡፡
ኤሚሬት እና እስራኤል የአብርሃም ስምምነትን በመፈረም ለዓመታት ሻክሮ የቆየ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ለማለስለስ መስማማታቸው ይታወሳል፡፡ በዚህም ሃገራቱ ኤምባሲዎቻቸውን ከፍተው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ማድረግ ጀምረዋል፡፡
ይህን የኤሚሬትን ፈለግ በመከተል ባህሬንይን ጨምሮ ሌሎች ሃገራት ከእስራኤል ጋር ያላቸውን ግንኙነት ማሻሻላቸው የሚታወቅ ነው፡፡