የዩክሬኑ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ድጋፍ ለማሰባሰብ በአፍሪካ ሀገራት ጉብኝት ሊያደርጉ ነው
የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ በዚህ ሳምንት በሚያደርጉት ጉብኝት ሶስት የአፍሪካ ሀገራትን ያዳርሳሉ
ከዩክሬን በርካታ ሸቀጦችን የሚያስገቡት የአፍሪከ ሀገራት በሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ገለልተኛ አቋምን እያንጸባረቁ ቀጥለዋል
የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ዲሚትሮ ኩሊባ በሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ዙርያ ለሀገራቸው ድጋፍ ለማሰባሰብ በዚህ ሳምንት ወደ አፍሪካ ሊያቀኑ መሆኑ ተገለጸ፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ በሁለት አመታት ወስጥ ለአራተኛ ጊዜ ወደ አፍሪካ በሚያደርጉት ጉዞ ማላዊ ፣ ዛምቢያ እና ማውርሺየስን ይጎበኛሉ ተብሏል፡፡
በቆይታቸውም ለሁለት አመታት በጦርነቱ ገለልተኛ አቋም በማንጸባረቅ የዘለቁትን የአፍሪካ ሀገራት ለዩክሬን ውግንናቸውን እንዲያሳዩ ለማሳመን ጥረት እንደሚያደርጉ ይጠበቃል፡፡
ዲሚትሮ ኩሊባ ጉዟቸውን አስመልክተው ባደረጉት ንግግር ሁሉም ስብሰባዎች በሁለትዮሽ እና የጋራ ጥቅምን ባከበረ መልኩ ይከናወናሉ ያሉ ሲሆን በተጨማሪም ለአፍሪካ ሀገራት የጥራጥሬ እና እህል ምርት አቅርቦቶችን ለመጨመር ከመሪዎች ጋር እንደሚመክሩ ተናግረዋል፡፡
ከሁለቱም ተፋላሚ ሀገራት ጋር ከፍተኛ የንግድ እና የዲፕሎማሲ ግንኙነት ያላት አፍሪካ በምዕራባውያን እና በዩክሬን ጦርነቱን እንድታወግዝ ከፍተኛ ጫና እያስተናገደች ብትገኝም ይፋዊ አቋም ከማንጸባረቅ ተቆጥባለች፡፡
ባሰለፍነው ወር ዩክሬን በሲውዘርላንድ ባዘጋጀችው የሰላም ጉባኤ ላይ የተሳተፉ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎችም በይፋ ጦርነቱን ከማውገዝ እና ሩሲያን ከመውቀስ ተቆጥበዋል፡፡
የአህጉሪቷ አብዛኛዎቹ ሀገራት ከዩክሬን ይልቅ ከሩሲያ ጋር ጠንካራ ወታደራዊ ፣ ዲፕሎማሲያዊ እና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት መፍጠራቸው በተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና በሌሎችም አለም አቀፍ መድረኮች ላይ ገለልተኛ አቋም እንዲያንጸባርቁ ዋነኛ ምክንያት እንደሆናቸው ይነገራል፡፡
አህጉሪቷ 50 በመቶ የሚሆነውን የስንዴ ምርት የምታስገባው ከሞስኮ እና ኬቭ ነው፡፡
ባሳለፍነው አመት መጋቢት ወር ላይ የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ በሩሲያ ላይ ጫና ለማሳደር ውሳኔ ሀሳብን ባሰለፈበት ስብሰባው በድምጽ ተአቅቦ ከወጡ 35 የአለም ሀገራት 17ቱ የአፍሪካ ሀገራት ናቸው፡፡
በዛሬው እለት ደግሞ የዩክሬን መንግስት በማሊ የሚንቀሳቀሱ ሽብረተኞችን እየደገፈ ነው ያለው የሀገሪቱ መንግስት ከዩክሬን ጋር ያለውን ዲፒሎማሲያዊ ግንኙነት በይፋ ማቋረጡን አስታውቋል፡፡
የሩስያው የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሰርጌ ላቭሮቭ የጦርነቱን መቀስቀስ ተከትሎ ኢትዮጵያ እና ኤርትራን ጨምሮ በ9 የአፍሪካ ሀገራ ተደጋጋሚ ጉብኝቶችን አድርገዋል፡፡
የዩክሬኑ አቻቸው ድሚትሪ ኩሊባ የአፍሪካውያንን ድጋፍ ለማሰባሰብ በሚደርጉት በዚህኛው ጉብኝታቸው ከእስከዛሬው የተለየ ጠንካራ ውግንናን ያገኛሉ ተብሎ ባይጠበቅም እያደገ የመጣውን የሞስኮ ተጽእኖ ለመቋቋም ዩክሬን ግንኙነቷን በወዳጅነት ማስቀጠሏ ወሳኝ ነው ተብሏል፡፡