ፖለቲካ
ዩክሬን ከጀርመን ተጨማሪ የአየር መቃወሚያ ማግኘቷን ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ አስታወቁ
ኪየቭ እገዛው ህዝቤን ከሩሲያ ሽብር ለመከላከል አስፈላጊ ነው ብላለች
የአየር መከላከያ መሳሪያው የሚመጡ ሚሳይሎችን ለማክሸፍ የተሰራ ነው ተብሏል
ጀርመንና ዩክሬን ተጨማሪ "ፓትሪዮት" የተባለ የአየር መቃወሚያ ሚሳይል ለኪየቭ ለመስጠት መስማማታቸው ተነግሯል።
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ከጀርመን መልካም ዜና መቀበላቸውን አስታውቀዋል።
"ዛሬ ከጀርመን ጥሩ ዜና አለ። ተጨማሪ 'የፓትሪዮት' ስርዓቶች ለማግኘት ተስማምተናል። ህዝባችንን ከሩሲያ ሽብር ለመከላከል አስፈላጊ ነው" ሲሉ ዘለንስኪ በተለመደው የምሽት መልዕክታቸው ተናግሯል።
ጀርመን ሁለት ተጨማሪ የመከላከያ መሳሪያ (ላውንቸር) ለዩክሬን እንደምትሰጥ አስታውቃለች።
ዘለንስኪ እርዳታው በእርግጠኝነት ለዩክሬን የአየር መከላከያ ለመፍጠር አጋዥ መሆኑን ጠቁመዋል።
ሮይተርስ እንደዘገበው እንደ "ፓትሪዮት" ያሉ የአየር መከላከያ መሳሪያዎች የሚመጡ ሚሳይሎችን ለመጥለፍ የተገነቡ ናቸው።
ሆኖም በኔቶ አጋሮች ከቀዝቃዛው ጦርነት በኋላ የአየር መከላከያ ክፍሎችን ማምረት በመቀነሳቸው የአቅርቦት እጥረት እንዳለ ተነግሯል።