አሜሪካ ለዩክሬን የ275 ሚልየን ዶላር ተጨማሪ ወታደራዊ ድጋፍ ልታደርግ ነው
ድጋፉ የመድፍ ተተኳሽ፣ ረዥም ርቀት ተምዘግዛጊ ሮኬቶችን የሚያካትት መሆኑ ታውቋል
የአሜሪካ ኮንግረስ በባለፈው ወር ለውጭ ሀገራት የሚደረጉ ወታደራዊ ድጋፎችን የያዘው 95 ቢልዮን ዶላር ረቂቅ እንዲዘገይ ማዘዙ ይታወሳል
ዩክሬን የሀገሪቷ ሁለተኛዋ ትልቅ ከተማ በሆነችው ካርኪቭ በሩስያ ጦር የተወሰደባትን ወታደራዊ ብልጫ ለመቋቋም ተጨማሪ የጦር መሳርያ እና የተተኳሾች ድጋፍ እንደሚያስፈልጋት በተደጋጋሚ ስትገልጽ ተደምጣለች።
ይህንን ተከትሎም አሜሪካ ለዩክሬን የመድፍ ተተኳሽ፣ ረዥም ርቀት ተምዘግዛጊ ሮኬቶችን የሚያካትት የ275 ሚልየን ዶላር ተጨማሪ ወታደራዊ ድጋፍ ልታደርግ መሆኑ ተሰምቷል
በተጨማሪም ድጋፉ ጃቭሊን እና ኤቲ-4 የተሰኙ የጸረ ታንክ ቴክኖሎጂዎችን፣ መሬት ላይ የሚቀበሩ ቦንቦች፣ ብረት ለበስ የውግያ ተሸከርካሪዎችንም ይዟል።
ባሳለፍነው ሰኞ 50 የአውሮፓ ሀገራት የጦር መሪዎች ወርሃዊ ስብሰባቸውን ባደረጉበት ወቅት የአሜሪካው የመከላከያ ሚንስትር ሎይድ ኦስቲን ሞስኮ በካርኪቨ የጀመረችው የተጠናከረ ዘመቻ ለኪቭ ሁኔታዎችን አሳሳቢ አድርጓል ብለዋል።
አክለውም ከምዕራቡ አለም የሚደረጉ የጦር መሳርያ ድጋፎች ቀጣይነት ከሌላቸው ሁኔታዎች ሊወሳሰቡ ይችላሉ ነው ያሉት።
አጃንስ ፍራንስ ፕረስ እንዳስነበበው ሞስኮ የኬቭን የሰው ሀይል እና የጦር መሳርያ እጥረት ዘመቻውን አጠናክራ ለመቀጠል፣ ወደፊት ለመገስገስ እየተጠቀመችበት ነው ።
የአሜሪካ ኮንግረስ በባለፈው ወር ለውጭ ሀገራት የሚደረጉ ወታደራዊ ድጋፎችን የያዘው 95 ቢልዮን ዶላር ረቂቅ እንዲዘገይ ማዘዙ ይታወሳል።
በአሜሪካው ፕሬዝዳንት ተፈርሞ በምክር ቤቱ እንዲዘገይ የተደረገው የውጭ ሀገራት ወታደራዊ ድጋፍ 95 ቢልዮን ዶላር ሲሆን ከዚህ ውስጥ ለዩክሬን 61 ቢልዮን ዶላር ድጋፍ መድቧል።
ረቂቁ ከዘገየ በኋላ ባይደን ከፔንታጎን የጦር ካዝናዎች 1.7 ቢልዮን ዶላር ግምት ያላቸው የጦር መሳርያዎችን ለዩክሬን ልከዋል።
ሩስያ በ2022 የካቲት ወር ላይ በዩክሬን ጦርነት ከጀመረች አንስቶ አሜሪካ የ51 ቢልዮን ዶላር ወታደራዊ ድጋፍ አድርጋለች ።
ምዕራባዊያን ሀገራት ከጦርነቱ መጀመር በኋላ የ380 ቢልዮን ዶላር ድጋፍ ለማድረግ ቃል የገቡ ሲሆን 118 ቢልዮን ዶላሩ በቀጥተኛ ወታደራዊ ድጋፍ የሚደረግ ነው።