ዩክሬን በጦርነቱ የሀገር ውስጥ መሳሪያዎችን መጠቀም መጨመሯን ባለስልጣናት ተናገሩ
ዩክሬን በጋራ ለማምረት እና ቴክኖሎጂ ለመቀያየር ከደርዘን በላይ ከሚሆኑ ሀገራት ጋር ተፈራርማለች
ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ የሀገር ውስጡ የመከላከያ ኢንዱስትሪ እንዲጠናከር ጥሪ አቅርበዋል
ዩክሬን በጦርነቱ የሀገር ውስጥ መሳሪያዎችን መጠቀም መጨመሯን ባለስልጣናት ተናገሩ።
ዩክሬን ከሩሲያ ጋር በምታደርገው ጦርነት በሀገር ውስጥ የተሰሩ መሳሪያዎችን እና ወታደራዊ ቁሳቁሶችን መጠቀም መጨመሯን አንድ ከፍተኛ የመከላከያ ባለስልጣን ተናግረዋል።
ከምዕራባውያን የጠየቀችው የመሳሪያ እርዳታ መዘግየቱን የምትገልጸው ዩክሬን በጦር መሳሪያ ምርት ራሷን ለመቻል አልማ እየሰራች መሆኑን ሮይተርስ ዘግቧል።
ዩክሬን ሁለት አመታትን ባስቆጠረው ጦርነት ሩሲያን እየተከላከለች ባለችበት ወቅት፣ ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ የሀገር ውስጡ የመከላከያ ኢንዱስትሪ እንዲጠናከር ጥሪ አቅርበዋል።
የዩክሬን ምክትል መከላከያ ሚኒስትር ኢቫን ለቭሪሉክ እንደገለጹት በፈረንጆች 2024 መጀመሪያ ሁለት ወራት በሀገር ውስጥ የተመረቱ 46 መሳሪያዎችን ለጦሩ ተልከዋል።
ይህ ከባለፈው አመት ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ጭማሪ አለው ያሉት ምክትል ሚኒስትሩ ዩክሬን "በጊዜ ሂደት ራሷን እንድትችል ሀሉንም ነገር እናደርጋለን" ብለዋል።
ዩክሬን በጋራ ለማምረት እና ቴክኖሎጂ ለመቀያየር ከደርዘን በላይ ከሚሆኑ ሀገራት ጋር ተፈራርማለች።
በዓለም ካሉት የታንክ እና የከባድ መሳሪያ ተተኳሽ አምራች ከሆኑት አንዱ የሆነው የጀርመኑ የመከላከያ ኩባንያ ሬይንሜታል በዩክሬን የተተኳሽ ፋብሪካ እንደሚከፍት ባለፈው ወር አሳታውቋል።
ኪቭ ባለፈው እሁድ 50 በመቶ የሚሆኑት ከዩክሬን አጋሮች የመጡት መሳሪያዎች መዘግየታቸውን ገልጻለች።
ዩክሬን በቅርቡ በምስራቅ ዩክሬን አቭዲቪካን ጨምሮ በርካታ ቦታዎችን የለቀቀችው የምዕራባውያን የጦር መሳሪያ እርዳታ በመዘግየቱ ነው ብላለች።