ዩክሬን በቅርቡ አሜሪካ ሰራሽ ረጅም ርቀት ተምዘግዛጊ ሮኬቶችን ልታገኝ ትችላለች ተባለ
ሩሲያ የአሜሪካ የጦር መሳሪያ ድጋፍ ጦርነቱን ይበልጥ ከማባበስ በዘለለ ምንም ጥቅም የሌለው ብላለች
ሮኬቶቹ እስከ 300 ኪሎ ሜትሮች ርቀት ድረስ ሊወነጨፉ የሚችሉ ናቸው ተብሏል
ዩክሬን በቅርቡ አሜሪካ ሰራሽ ረጅም ርቀት ተምዘግዛጊ ሮኬቶችን (MLRS) ልታገኝ ትችላለች ተባለ፡፡
ሆኖም ሮኬቶቹ ድንበር ተሻግረው ሩሲያ ለመምታት የሚችሉ እንደማይኑ ዋሽንግተን አስታውቃለች፡፡
ሩሲያ በምስራቃዊ የሃገሪቱ አካባቢ የጀመረችው የተጠናከረ ዘመቻ ያሳሰባት የምትመስለው ዩክሬን ከሰሞኑ ረጅም ርቀት ዒላማዎችን ለመምታት የሚችሉ ጦር መሳሪያዎች ድጋፍ እንዲደረግላት አሜሪካን ጨምሮ ምዕራባውያንን ጠይቃ ነበረ፡፡
የፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ አማካሪ እና የሰላም ተደራዳሪ ማይካሂሎ ፖዶሊያክ “በአሜሪካ የተሰሩ የረዥም ርቀት ባለብዙ ሮኬት ማስወንጨፊያዎች ያስፈልጉናል” ሲሉም ነበር በወቅቱ ጥሪ ያቀረቡት።
ጥሪውን ተከትሎም አሜሪካ ረጅም ርቀት ተምዘግዛጊ ሮኬቶችንና ማስወንጨፊያዎችን ለዩክሬን እንደምትሰጥ አስታውቃለች፡፡
ይሁን እንጂ ፕሬዝዳንት ባይደን ሩሲያ ሊደርሱ የሚችሉ ሮኬቶችን ወደ ዩክሬን አንልክም ብለዋል፡፡
ሩሲያም ብትሆን ስለ ጦር መሳሪያዎቹ ድጋፍ ዝም አላለችም፡፡ ድጋፉ ጦርነቱን ይበልጥ ከማባበስ በዘለለ ምንም ጥቅም የለውም ስትል ዋሽንግተንን ወቅሳለች፡፡
የአሜሪካ የጦር መሳሪያ ድጋፍ፤ የጦርነቱን መጠን በማስፋት የኔቶ አባል ሀገራትን ወደ ጦርነቱ እንዳያስገባ ተሰግቷል፡፡
የሩሲያ ኃይሎች በአሁኑ ወቅት በዶንባስ ግዛት የሚገኙትን ሰቬሮዶኔስክና ሌሎችንም አካባቢዎች በከባድ መሳሪያዎች በመደብደብ ላይ ይገኛሉ፡፡
ዩክሬን ከአሁን በፊት ከአሜሪካ 'ኤም-777 ሃዊትዘርስ' የተባለና 25 ኪሎ ሜትሮችን የሚምዘገዘግ ሮኬት ማግኘቷ የሚታወስ ነው፡፡
አሁንም በድጋፍ መልክ እንደምታገኘው የተነገረለት ረጅም ርቀት ተምዘግዛጊ ሮኬት እስከ 300 ኪሎ ሜትሮች ድረስ ተምዘግዝጎ ዒላማዎቹን ለመምታት የሚያስችል ባትሪ የተገጠመለት ነው ተብሏል፡፡
ብሪታኒያም ብትሆን አሉኝ ያለቻቸውን ተመሳሳይ ሮኬቶች ለዩከሬን ለመስጠት ዝግጁ መሆኗን ገልጻለች፡፡
አሜሪካ 'ኤም.ኤል.አር.ኤስ' ሮኬቶችን እ.ኤ.አ ከ1990-91 በተካሄደው የኢራቅ ጦርነት ግልጋሎት ላይ ማዋሏ ይነገራል፡፡