ዩክሬን በአሜሪካ የተሰሩ የረጅም ርቀት ሮኬቶች እንደሚያስፈልጓት ገለጸች
የሩሲያ ኃይሎች በምስራቅ ዩክሬን የሚያደርጉት ወታደራዊ ግስጋሴ አጠናክረው መቀጠላቸው እየተገለጸ ነው
የዩክሬን ፖሊስ "ሲየቪዬሮዶኔትስክ ከተማ በማያቋርጥ የጠላት ጥይት እየተደበደበች ነው" ብለዋል
የሩሲያ ኃይሎች በምስራቅ ዩክሬን የሚያደርጉት ወታደራዊ ግስጋሴ አጠናክረው መቀጠላቸው ተገለጸ፡፡
የሩሲያ ኃይሎች እስካሁን በሲቪዬሮዶኔትስክ ከተማ አቅራቢያ የሚገኘውን የሊማን የባቡር ማእከል የያዙ ሲሆን በምስራቅ ዩክሬን ተጨማሪ ወታደራዊ ይዞታዎች ለመቆጣጠር መጠነ ሰፊ ጥቃት እየሰነዘሩ ነው ተብለዋል፡፡
ጥቃቶቹ መቋቋም የከበዳት የምትመስለው ዩክሬን በበኩሏ ተጨማሪና ረዥም ርቀት የሚምዘገዘጉ የጦር መሳሪያዎች ያስፈልገኛል ስትል ምዕራባውያንን ጠይቃለች፡፡
የዩክሬን ፕሬዝዳንት አማካሪ እና የሰላም ተደራዳሪ ማይካሂሎ ፖዶሊያክ “በአሜሪካ የተሰሩ የረዥም ርቀት ባለብዙ ሮኬት ማስወንጨፊያዎችን ያስፈልጉናል” ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
ፖዶሊያክ በትዊተር ገጻቸው ባጋሩት መልእክት "ከ 70 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ጥቃት ሲሰነዘርብህ ለመዋጋት አስቸጋሪ ነው፤ ዩክሬን ተወንጫፊ መሳሪያዎች ቢኖሯት ኖሮ ሩሲያን ከብረት መጋረጃ ጀርባ መመለስ ትችላለች፤ ነገር ግን ለዚያ ውጤታማ መሳሪያዎች እንፈልጋለን "ም ብለዋል፡፡
ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘሌንስኪ፤ የዩክሬን አጋሮች አስፈላጊውን መሳሪያ እንደሚያቀርቡ ያላቸውን ተስፋ ግለጸዋል፡፡በዚህ ሳምንት "የምስራች እጠብቃለሁ"ም ነው ያሉት ዘሌንስኩ።
የአሜሪካ ባለስልጣናት በበኩላቸው ያለውን ሁኔታ በቅርበት እየተከታተልነው ነው እናም “በቅርብ ቀናት ውሳኔ ሊኖር ይችላል” ማለታቸው ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ከጊዜ አንጻር የዘገየ ግን ደግሞ ጠንካራ ነው የተባለለት የሩሲያ ኃይሎች የምስራቅ ዩክሬን ግስጋሴ የሉሃንስክ እና የዶኔትስክ ግዛቶችን ለመቆጣጠር ያለመ ሲሆን፤ ሙሉ በሙሉ የሚሳካ ከሆነ ሩሲያ የጦርነቱን የበላይነት በአስተማማኝ መልኩ እንድታረጋግጥ ያስችላታል እየተባለ ነው፡፡
በገጠማቸው ጠንካራ የአጸፋ ምት ኪቭን በቀላሉ መቆጣጠር እንዳልቻሉ የሚነገርላቸው የሩሲያ ኃይሎች አሁን ላይ ባላት ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታ ወሳኝ የሂነቸውን የሉሃንስክን ግዛት ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር የተቃረቡ ይመስላሉ፡፡
የሩስያ መከላከያ ሚኒስቴር ፤ የሩሲያ ኃይሎች እና አጋሮቻቸው የሆኑ ተገንጣይ ሃይሎች በዲኔትስክ፤ ከሲቨርስኪ ዶኔትስ ወንዝ በስተ ምዕራብ የሚገኘው የባቡር መጋጠሚያ የሚገኘውን ሊማንን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥረዋል ብለዋል፡፡
ሆኖም የዩክሬን ምክትል የመከላከያ ሚኒስትር ሃና ማሊያር የሊማን ጦርነቱ እንደቀጠለ ነው መላታቸውን የዜን.ዋ ድረ-ገጽ ዘግቧል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የዩክሬን ፖሊስ "ሲየቪዬሮዶኔትስክ በማያቋርጥ የጠላት ጥይት እየተደበደበች ነው" ሲል በማህበራዊ ሚዲያው አጋርቷል።
የሉሃንስክ ገዥ ሰርሂ ጋይዳይ የሩሲያ ወታደሮች ወደ ሲቪዬሮዶኔትስክ መግባታቸውን ተናግረዋል ።
የዩክሬን ወታደሮች እንዳይያዙ ከከተማዋ ማፈግፈግ ሊኖርባቸው ይችላል ሲሉም አክሏል ጋይዳይ።