የሉሃንስክን ግዛት ያጣው የዩክሬን ሃይል ዶኔትስክን ለመከላከል ተሰባሰበ
ዩክሬን ተወስደውብኛል የምትላቸውን ግዛቶች ለማስመለስ እንምትንቀሳቀስ ገልጻለች
ፕሬዝዳንት ፑቲን የሩሲያ ጦር ማጥቃቱን እንዲቀጥል አዘዋል
አምስት ወራት ባስቆጠረው የዩክሬን-ሩሲያ ጦርነት፤ የሩሲያ ኃይሎች ቁልፍ የሚባለውን የሉሃንስክ ግዛት መቆጣጠራቸውን አስታውቀዋል፡፡ፕሬዝዳንት ፑቲን ሉሃንስክን የተቆጣጠሩት ወታደረሮች እንደሚሸለሙ የገለጹ ሲሆን የሩሲያ ጦር ዶንባስን ለመቆጣጠር ማጥቃቱን ይቀጥላል ብለዋል፡፡
ሩሲያ በሉሃንስክ ግዛት የሚገኙትን የሴቭሮዶኔስክ እና ሊሲቻንስክ ከተማ በመቆጣጠር ነበር ግዛቱን ሙሉሙሉ በሩሲያ ስር መውደቁን ያሳወቀችው፡፡
በግዛቱ በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል የተካሄደው ጦርነት በሁለቱም ወገን ትልቅ ጉዳት ማስከተሉን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ሁለቱም ወገኖች ለሉሃንስክ በተደረገው ውጊያ በተለይም በሊሲቻንስክ እና በሲዬዬሮዶኔትስክ መንትያ ከተሞች በተከበቡበት ወቅት ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል። ሁለቱም ከተሞች ፋታ በሌለው የሩስያ የቦምብ ጥቃት ፈርሰዋል።
በመካከለኛው ዲኒፕሮ ከተማ ለመጠለል ከሊሲቻንስክ የሸሸች አንዲት ወጣት እናት ኒና “ከተማዋ ከእንግዲህ የለችም” ስትል ለሮይተርስ ተናግራለች።
“በተግባር ከምድር ገጽ ላይ ተጠርጓል። ምንም አይነት የሰብአዊ እርዳታ ማከፋፈያ ማዕከል የለም፤ ወድሟል፡፡ ማዕከሉን ይይዝ የነበረው ሕንፃ ከዚህ በኋላ የለም። ልክ እንደ ብዙዎቹ ቤቶቻችን።
ግጭቱ ከተቀሰቀሰበት ጊዜ ጀምሮ ሩሲያ ዩክሬንን ሉሃንስክን እና ዶኔትስክን ለሞስኮ ደጋፊ ተገንጣዮች አሳልፋ እንድትሰጥ ስትጠይቅ ቆይታለች፤አሁን ላይ ሩሲያ ሁለቱ ግዛቶች ራሳቸውን የቻሉ ነጻ ግዛቶች ናቸው ስትል አውጃለች፡፡
የፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዘሌንስኪ አማካሪ ኦሌክሲይ አሬስቶቪች “ይህ በዩክሬን ግዛት ላይ ለሩሲያ የመጨረሻው ድል ነው” ብለዋል ።
አሬስቶቪች እንደተናገሩት ከዶኔትስክ ጦርነት በተጨማሪ ዩክሬን በሀገሪቱ ደቡብ የመልሶ ማጥቃት ዘመቻ እንደምትጀምር ተስፋ አድርጋ ነበር።
ዩክሬን ተወስደውብኛል የምትላቸውን ግዛቶች ለማስመለስ እንምትንቀሳቀስ ገልጻለች፡፡