"በቤላሩስ የምናደርገው ድርድር የለም" - የዩክሬን ፕሬዝዳንት
የቤላሩሱ ፕሬዝዳንት ድርድሩን በተሳካ ሁኔታ ለማካሄድ አስፈላጊውን ሁሉ አመቻቸለሁ ብለው ነበር
ሩስያ ተደራዳሪ ቡድን ወደ ቤላሩስ ብትልክም ዩክሬን ሳትቀበለው ቀረች
ሩስያ ተደራዳሪ ቡድን ወደ ቤላሩስ ብትልክም ዩክሬን ሳትቀበለው ቀረች፡፡
ወደ ቤላሩስ ያቀናው የሩሲያ ልዑክ ከሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ፣ የመከላከያ ሚኒስቴር እና ከተለያዩ የመንግስት ተቋማት የተውጣጡ ተደራዳሪ አካላትን መያዙን የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሜትሪ ፔስኮቭ ተናግረዋል፡፡
ለድርድሩ ስኬታማነት አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርጉም የሩስያ ጠንካራ አጋር እንደሆኑ የሚነገርላቸው የቤላሩሱ ፕሬዝዳንት አሌክሳንደር ሉካሼንኮ ቃል ገብተዋል፡፡
ሆኖም ዩክሬን ድርድሩን ሳትቀበል ቀርታለች፡፡ ወደ ሚኒስክ የላከችው ልዑክም የለም፡፡
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ባስተላለፉት የቪዲዮ መልዕክት "በቤላሩስ የምናደርገው ድርድር የለም" ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ በመልዕክታቸው እንዳሉት ከሆነ ሩሲያ በዩክሬን ላይ ለከፈተችው ጥቃት ግዛቷን ክፍት አድርጋ ዩክሬን እንድትመታ ባደረገችው ቤላሩስ ለይ የሚደረግ ድርድር አይኖርም፡፡
ከሚኒስክ ውጭ በሌሎች ቦታዎች ለመደራደር ዝግጁ ነን ያሉት ዜሌንስኪ “ጦርነቱ ቆሞ ሰላም እንዲወርድ እንፈልጋለን፤ በዋርሶ፣ በብራቲስላቭ፣ በቡዳፔስት፣ በኢስታንቡል እንዲሁም ባኩን በመሳሰሉ ከተሞች መገናኘት እንደምንችልም አሳውቀናል” ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ሆኖም ዲሜትሪ ፔስኮቭ ቤላሩስን ለንግግር የመረጡት ራሳቸው ዩክሬናውያን መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ጦርነቱ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ቀልብ እንደሳበ ቀጥሏል፡፡ ሩሲያ ሉዓላዊ ሃገር የሆነችውን ዩክሬንን ወራለች በሚል ድርጊቱን የሚያወግዙት አሜሪካን ጨምሮ ምዕራባዊ አጋሮቿ የተለያዩ የማዕቀብ ናዳዎችን በሞስኮው ላይ እያዘነቡ ነው፡፡
የበረራ እና የፋይናንስ እንቅስቃሴዎችን ከማገድ ባለፈ ‘ስዊፍት’ ከተሰኘው ዓለም አቀፍ የበይነ-ባንክ ስርዓት (Swift interbank system) ሩሲያን ማገዳቸውን አስታውቀዋል፡፡
የሩሲያ ብሔራዊ ባንክን ጭምር የሚመለከተው ይህ እርምጃ በመጪዎቹ ቀናት ተግባራዊ ይደረጋል የተባለ ሲሆን በዓለም አቀፍ ግብይቶች የሚኖራትን የፋይናንስ እንቅስቃሴ ለመግታት ያስችላል ተብሎለታል፡፡
የአየር እና የነዳጅ ጣቢያዎችን ዒላማ ያደረገ መጠነ ሰፊ ጥቃት በዩክሬን በመፈጸም ላይ የሚገኘው የሩሲያ ጦር ወደ ሁለተኛዋ ትልቅ የዩክሬን ከተማ ካርኪቭ መግባቱን ዛሬ አስታውቋል፡፡
ዩክሬን ለዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት (ICJ) አቤት ማለቷን ፕሬዝዳንቷ አስታውቀዋል፡፡ ሩሲያ ጅምላ ጭፍጨፋን ተገን አድርጋ በፈጸመችብን ወረራ መጠየቅ አለባትም ብለዋል ፕሬዝዳንቱ፡፡ ወረራውን እንድታቆም የሚያስገድድ አስቸኳይ ውሳኔ እንዲሰጥ ጠይቀናልም ብለዋል ዘሌንስኪ ጉዳዩ በመጪው ሳምንት መታየት ይጀምራል ብለው እንደሚጠብቁ በማስታወቅ፡፡