የዩክሬን ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ የመኪና አደጋ ደረሰባቸው
ፕሬዝደንት ዘሌሰንኪ ወታደሮቻቸው በመልሶ ማጥቃት 2 ሺህ ስኩዌር ኪሎ ሜትር ቦታ ከሩሲያ ነጻ መውጣቱን ተናግረዋል
ፕሬዝዳንት ቮሊድሚር ዘለንስኪ ጦራቸው ከሩሲያ ያስለቀቃቸውን ስፍራዎች ጎብኝተው ሲመለሱ ነው አደጋው ያጋጠመው
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሊድሚር ዘለንስኪ የመኪና ግጭት አደጋ እንደደረሰባቸው ቃል አቀባያቸው ይፋ አድርገዋል።
ፕሬዚዳንቱ በኪቭ ከተማ ውስጥ በእጀባ በመጓዝ ላይ እያሉ ያሉበት መኪና ከመንገደኛ መኪና ጋር መጋጨቱን የፕሬዝዳቱ ቃል አቀባይ ሰርጉ ነይክሪፎቭ ባጡት መግለጫ አስታውቀዋል።
ከአደጋው በኋላ ፕሬዝዳንቱ በዶክተሮች እንደታዩ እና ከባድ ጉዳት እንዳልደረሰባቸው መረጋገጡንም ቃል አቀባዩ አስታውቀዋል።
ከፕሬዝዳንቱ መኪናጋር የተጋጨው አሽከርካሪ በስፍራው የህክምና ክትትል ከተደረገለት በኋላ በአምቡላንስ ወዳልታወቀ ስፍራ እንደተወሰደም ቢቢቢ ዘግቧል።
የመኪና አደጋው ሁኔታ በህግ አስከባሪ አካላት ምርመራ እየተደረገበት መሆኑን ሰርጉ ነይክሪፎቭ አስታውቀዋል።
ፕሬዝዳንት ቮሊድሚር ዘለንስኪ ጦራቸው ከሩሲያ ነጻ በማውጣት የተቆጣጠራትን ኢዚየም ከተማን ጎብኘተው ሲለመሱ እንደሆነም ታውቋል።
ፕሬዝደንት ቮሎዲሚር ዜለንስኪ ባሳለፍነው ሳምንት በሰጡት መገለጫ፤ ወታደሮቻቸው በወሰዱት የመልሶ ማጥቃት እርምጃ “2 ሺህ ስኩዌር ኪሎ ሜትር ቦታ ከሩሲያ ነጻ መውጣቱ” ተናግረዋል።
የዩክሬን ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ዲሚትሮ ኩሌባ ፤ እየተገኙ ያሉ ድሎች የዩክሬን ኃሎች የሩሲያ ጦርን ማሸነፍ እንደሚችሉ አማላካች ናቸው ብለዋል።
ጦርነቱ በፍጥነት እንዲጠናቀቅ ምዕራባውያንና የዩክሬን አጋሮች የሚያደርጉት የጦር መሳሪያ ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉበት ሲሉም ተማጽነዋል።