ዩክሬን ለመልሶ ማጥቃት መዘጋጀቷን የሀገሪቱ ከፍተኛ የደህንነት ሃላፊ ተናገሩ
የብሄራዊ ደህንነት ምክርቤት ዋና ጸሃፊው ኦሌክሲ ዳኒሎቭ ፥ ኬቭ በሩሲያ የተያዙባትን ይዞታዎቿን ለማስለቀቅ ተዘጋጅታለች ብለዋል
ሩሲያ በበኩሏ “ታክቲካል” ኒዩክሌር መሳሪያዎቿን ወደ ቤላሩስ ማስገባት ጀምራለች
ዩክሬን በሩሲያ ሃይሎች ላይ መልሶ ማጥቃት ለመክፈት ዝግጅቷን ማገባደዷን የሀገሪቱ ከፍተኛ የደህንነት ሃላፊ ገልጸዋል።
የመልሶ ማጥቃት እርምጃውን ለማካሄድ ለወራት ስትዘጋጅ የቆየችው ኬቭ ዘመቻውን “ዛሬ ወይም ነገ አልያም በሳምንታት ውስጥ ትጀምራለች” ብለዋል የዩክሬን የደህንነት እና መከላከያ ምክርቤት ዋና ጸሃፊ ኦሌክሲ ዳኒሎቭ።
ሃላፊው “ታሪካዊ አጋጣሚ” እና “ልናጣው የማይገባ ነው” ያሉትን የመልሶ ማጥቃት ዘመቻ ውሳኔ የቮልድሚር ዜለንስኪ መንግስት አስቁሞት ስህተት የመስራት መብት እንደሌለውም ነው የገለጹት።
የብሄራዊ ደህንነት ምክርቤት ጸሃፊው በፕሬዝዳንት ዜለንስኪ የጦር ካቢኔ ውስጥ ትልቅ ስፍራ እንዳላቸው ይነገራል።
ከቢቢሲ ጋር እያደረጉት የነበረው ቃለመጠይቅም ከፕሬዝዳንቱ በደረሳቸው የጦርነት እቅድ ስብሰባ መስተጓጎሉ ተገልጿል።
የዋግነር ቅጥረኛ ወታደራዊ ቡድን ከባክሙት እየወጣ መሆኑን ያነሱት ዳኒሎቭ፥ ቡድኑ ከከተማዋ እየወጣ ቢሆንም በሶስት የተለያዩ አካባቢዎች ዩክሬንን ለመውጋት እየተዘጋጀ መሆኑን አብራርተዋል።
ሞስኮ ወደ ቤላሩስ የኒዩክሌር መሳሪያዎቿን መላክ መጀመሯንም ሀገራቸው በጥብቅ እንደምትከታተለው ነው በቃለመጠይቁ ያነሱት።
ዩክሬን በሩሲያ የተያዙባትን አካባቢዎች ለማስለቀቅ ለወራት ወታደሮቿን በማሰልጠንና የምዕራባውያኑን ወታደራዊ ድጋፍ በመጠባበቅ አሳልፋለች።
አሜሪካን ጨምሮ አጋሮቿ ቃል የገቡላትን ድጋፍ በፍጥነት እንዲያቀርቡ ስትወተውትም ቆይታለች።
የዩክሬን የደህንነት እና መከላከያ ምክርቤት ዋና ጸሃፊ ኦሌክሲ ዳኒሎቭ “የመልሶ ማጥቃት ልንከፍት ነው” አስተያየትም የዝግጅቷ ማሳያ ተደርጎ ተወስዷል።
ሩሲያ በበኩሏ “ታክቲካል” ኒዩክሌር መሳሪያዎቿን ወደ ቤላሩስ ማስገባት መጀመሯ ተነግሯል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደንም ይህንኑ እርምጃ የተቃወሙ ሲሆን፥ ሞስኮ ግን ዋሽንግተን በአውሮፓ ሀገራት ታክቲካል የኑዩክሌር መሳሪያዎቿን አከማችታ ወደ ክሬምሊን ጣት መቀሰር አትችልም ብላለች።
በአሜሪካ የሚገኘው የሩሲያ ኤምባሲ፥ “ሩሲያ ለተቃጣባት ቅይጥ ጦርነት ምላሽ ለመስጠት ከቤላሩስ ጋር መተባበሯ ተገቢ ነው” ማለቱንም አርቲ አስነብቧል።