ዩክሬን በጦርነቱ አብዛኞቹ ኤርፖርቶቿ እንደወደሙባት ገለጸች
ዩክሬን 20 የሲቪል አውሮፕላን ማረፊያዎች ያሏት ሲሆን የተወሰኑትን ክፍት የምታደርግበትን መንገድ እየፈለገች ነው

በአሁኑ ወቅት ወደ ውጭ መሄድ የሚፈልጉ ዩክሬናውያን በአውሮፕላን የሚሳፈሩት በባቡር ወይም በመንገድ ወደ ጎረቤት ሀገራት ከሄዱ በኋላ ነው
ዩክሬን በጦርነቱ አብዛኞቹ አውሮፕላን ማረፊያዎቿ እንደወደሙባት ገለጸች።
ሩሲያ በዩክሬን ላይ ልዩ ያለችውን ዘመቻ ከከፈተችበት ከየካቲት 2022 ጀምሮ 15 የሚሆኑ ኤርፖርቶቿ እንደወደሙባት የዩክሬን ጠቅላይ ሚኒስትር ዴኒስ ሽምይሀል መናገራቸውን ሮይተርስ የሀገሪቱን ሚዲያዎች ጠቅሶ ዘግቧል።
ዩክሬን 20 የሚሆኑ የሲቪል ኤርፖርቶች ያሏት ሲሆን የተወሰኑትን ክፍት የምታደርግበትን መንገድ እየፈለገች ነው። አውሮፕላን ማረፊያዎቹ ከጦርነቱ መጀመር በኋላ ተዘግተው ቆይተዋል።
በአሁኑ ወቅት ወደ ውጭ መሄድ የሚፈልጉ ዩክሬናውያን በአውሮፕላን የሚሳፈሩት በባቡር ወይም በመንገድ ወደ ጎረቤት ሀገራት ከሄዱ በኋላ ነው።
"የአደጋ ሁኔታዎችን ግምገማ አጠናቀናል፤ የአየር ኃይሉ የአየር ክልሉን በከፊል ክፍት መደረግ እንዳለበት ወስነናል"ብለዋል ሽምይሀል።
ሽምይሀል አክለውም እንደገለጹት "የጸጥታ እና ወታደራዊ ሁኔታዎች ለዚህ ውሳኔ ቁልፍ ናቸው።"
ሸምይሀል ሩሲያ የዩክሬን የወደብ መሰረተልማቶችን 60 ጊዜ በማጥቃት 300 ተቋማትን እና 22 የሲቪል መርከቦችን አውድማለች ብለዋል።
ተቆጣጣሪዎች ደህንነት የተጠበቀ መሆኑን ካረጋገጡ እና የፖለቲካ ውሳኔ ከተወሰነ፣ ዩክሬን በ2025 በምዕራብ ዩክሬን ሊቪቭ የሚገኘውን ኤርፖርት ለአገልግሎት ልትከፍት ትችላለች ተብሏል።
የአሜሪካው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ዩክሬን የረጅም ርቀት ሚሳይሎችን ሩሲያ ውስጥ ያሉ ኢላማዎችን እንድትመታ መፍቀዳቸው እና ይህን ተከትሎ ሩሲያ ኦርሽኒክ የተባለ የመካከለኛ ርቀት ሚሳይል ወደ ዩክሬን ማስወንጨፏ ጦርነት ጡዘት ላይ ደርሷል።
ምዕራባውያን ለዩክሬን የኑክሌር ጦር መሳሪያ ሊያስታጥቁ ይችላሉ የሚሉ ዘገባም በቅርቡ ወጥቶ ነበር። ፑቲን ዩክሬን የኑክሌር ጦር መሳሪያ የምትታጠቅ ከሆነ ሩሲያ በኑክሌር ጦር መሳሪያ መልስ ከመስጠት ውጭ አማራጭ እንደማይኖራት አስጠንቅቀዋል።