ዩክሬን ከ400 ካሬ ኪሎ ሜትር በላይ የሚሆነውን የኬርሶን ግዛት ቦታ መልሳ መያዟን አስታወቀች
የኬርሶን ክልል በቅርቡ በፑቲን ፊርማ ወደ ሩሲያ ከተቀላቀሉት ግዛቶች አንዱ መሆኑ ይታወቃል
የክሬምሊን ቃል አቀባይ፤ ረሲያ የምትለቀውን ማንኛውም ግዛት መልሳ ትይዛለች ሲሉ ተደምጠዋል
ዩክሬን፤ ሞስኮ ተቆጣጠርኩት ያለችውን የኬርሶን ግዛት ከአንድ ሳምንት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ ስፋት ያለው ቦታ መልሳ መያዟን አስታወቀች።
የዩክሬን ደቡባዊ ጦር አዛዥ ቃል አቀባይ ናታልያ ጉሜኒዩክ በኦንላይን ባደረጉት አጭር መግለጫ ፤ “ከ400 ካሬ ኪሎ ሜትር (155 ካሬ ኪሎ ሜትር) በላይ የሚሆነውን የኬርሰን ክልል ነጻ አውጥተናል” ብለዋል።
ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ ቆየት ብለው በሰጡት አስተያየት ዩክሬን ተጨማሪ ሶስት መንደሮችን ነጻ ማውጣቷን ገልጸዋል።
ዘለንሰኪ ይህን ይበሉ እንጅ የክሬምሊን ባለስልጣናት ግን፤ “ድሉ ጊዜያዊ ነው በዩክሬን ምድር የፈለግነውን ዓላማ ከማሳካት የሚያግደን ኃይል የለም” እያሉ ነው።
የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ “ሩሲያ ተሸንፋ የምትለቀውን ማንኛውም ግዛት መልሳ ትይዛለች” ሲሉ ተደምጠዋል።
በአዳዲሶቹ ግዛቶች ሩሲያ እየደረሰባት ያለውን ሽንፈት በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ “እስከመጨረሻው ከሩሲያ ጋር ይቆያሉ፤ ይመላሳሉ” ብለዋል ኤኤፍፒ ዘግቧል።
ሩሲያን ተቀላቅለዋል በተባሉት አዳዲስ ግዛቶች በወታደራዊ ዘመቻቸው ኪሳራን እያስተናገዱ ያሉት ፑቲን ከዩክሬን የጠቀለሏቸውን አራት ግዛቶች የሩሲያ አካል መሆናቸውን የተመለከተው ሰነድ ላይ በትናትናው እለት የመጨረሻውን ፊርማ ማኖራቸው አይዘነጋም።
ፑቲን የፈረሙበት ሰንድ ሉሃናስክ፣ ዶንቴስክ፣ ዛፖርዚያ እና ኬርሶን የተባሉት የቀድሞ የዩክሬን ግዛቶች “ከሩሲያ ፌዴሬሽን ጋር ለመቀላቀል ወስነዋል” የሚል ነው።
ሆኖም የዩክሬን ጦር በሁለቱ ግዛቶች [ሉሃንስክ እና ኬርሶን] ስር ያሉ መንደሮችን መልሼ መቆጣጠር ችያለሁ እያለ ነው።
በተጨማሪም ፑቲን በዛፖርዚያ ግዛት ያለውን የኒውክሌር ጣቢያ ሩሲያ እንደወረሰችው የሚገልጽ አዋጅንም በፊርማቸው አጽድቀዋል።
ባለፈው አርብ የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቢሯቸው በተካሄድ ስነሰርዓት ላይም በሞስኮ በተሾሙ ከአራቱ አዳዲስ ግዛቶች መሪዎች ጋር ስምምነት ተፈራርመዋል።