ፕሬዝዳንት ዘሌንስኪ ዩክሬን የ2030 የአለም ዋንጫን ለማዘጋጀት የሚያስችል ሂደት እንድትጀምር ፍቃድ ሰጥተዋል
ከሩሲያ ጋር ጦርነት ከገጠመች ሰባት ወራትን ያስቆጠረችው ዩክሬን የ2030 የዓለም ዋንጫን ጨዋታዎችን ለማስተናገድ የሚያስችላልትና በርካቶችን ያስገረመ ውሳኔ ማሳለፏ ተገለፀ።
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሊድሚር ዘለንስኪ ሀገራቸው ከስፔን እና ከፖርቹጋል ጋር በጋራ በመሆን የ2030 የዓለም ዋንጫ አስተናጋጅነት ውድድርን እንድትቀላቀል የሚያስችል ፈቃድ መስጠታቸውንም የብሪታኒያው ታይም ጋዜጣ አስነብቧል።
ዩክሬን የዓለም ዋንጫን ለማዘጋጀት ፍላጎት እንዳላትም በነገው እለት በአውሮፓ የእግር ኳስ ማህበር ዋና መስሪያ ቤት ይፋ እንደሚደረግም ታውቋል።
ዩክሬን "እግር ኳስ ተስፋን እና ሰላምን ይመልሳል" በሚል ሀሳብ ውድድሩን ለማዘጋጀት ማቀዷንም የታይምስ ጋዜጣ ዘገባ ያመለክታል።
ምንም እንኳን የዓለም ዋንጫን ለማዘጋጀት ሰላም ወሳኝ ቢሆንም፤ እስከ 2030 ድረስ ዩክሬን ከሩሲያ ጋር የገባቸው ጦርነት ተጠናቆ ሀገሪቱ ወደ መልሶ ግንባታ ትገባለች በሚል ተስፋ ውድድሩን ለማስተናገድ ማቀዷም ተመላክቷል።
ዩክሬን የዓለም ዋንጫን ለማስተናገድ ለውድድር መቅረቧን ተከትሎም በ211 የፊፋ አባል ሀገራት ዘንድ ከፍተኛ ድምጽ እንድታገኝ ሊያደርግ እንደሚችልም ከወዲሁ ከፍተኛ ግምት ተሰጥቷታል።
የ2022 የዓለም ዋንጫ ፊታችን ህዳር ወር ላይ በኳታር አስተናጋጅነት መካሄድ እንደሚጀምር ይጠበቃል።