ዩክሬን በሩሲያ የወደመባትን የኃይል መሰረተልማት ለመጠገን 18 ወራት ሊወስድ ይችላል አለች
ፕሬዝደንት ዘለንስኪ እንዲህ አይነት የአየር ጥቃት ለመከላከል ምን እንደሚያስፈልገን ሁሉም ያውቃል ሲሉም ተናግረዋል
ተቋሙ ጉዳት የደረሰባቸውን ጣቢያዎች ለመጠገን 18 ወራት ሊፈጅ ይችላል ብሏል
ዩክሬን በሩሲያ የወደመባትን የኃይል መሰረተልማት ለመጠገን 18 ወራት ሊወስድ ይችላል አለች።
የዩክሬኑ ግዙፍ የኃይል ተቋም(ዲቴክ) ሩሲያ ለሁለት ሳምንታት ባደረሰችው ጥቃት ከስድስቱ የኃይል ጣቢያዎች ውስጥ አምስቱ መጎዳታቸውን ወይም መውደማቸውን አስታውቋል።
በጥቃቱ ዩክሬን 80 በመቶ የኃይል አቅሟን ማጣቷን የገለጸው ተቋሙ ጉዳት የደረሰባቸውን ጣቢያዎች ለመጠገን 18 ወራት ሊፈጅ ይችላል ብሏል።
ሩሲያ ባለፈው አርብ ባደረሰችው ጥቃት በማዕከላዊ እና በምዕራብ ዩክሬን በሚገኙ የእንፏለት ኃይል ወይም የተርማል እና የውሃ ኃይል ማመንጫዎች ላይ ጉዳት ደርሷል።
የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ባለፈው ቅዳሜ ምሽት ባስተላለፉት የቪዲዮ መልእክት ሩሲያ የዩክሬንን መሰረተልማት ለማውደም ያለመ የአየር ድብደባ እያካሄደች ነው ብለዋል።
"አሜሪካ፣ አውሮፓ እና ሌሎች ሀገራት ምን እንደምንፈልግ ያውቃሉ" ብለዋል ዘለይስኪ።
ፕሬዝደንት ዘለንስኪ እንዲህ አይነት የአየር ጥቃት ለመከላከል ምን እንደሚያስፈልገን ሁሉም ያውቃል ሲሉም ተናግረዋል።
የሀገሪቱን 1/4 የሚሆነውን የሀይል አቅርቦት የሚሸፍነው ዲቴክ የተርማል እና ሌሎች ጣቢያዎቹ በሩሲያ ድሮኖች እና ሚሳይሎች ለሁለት ተከታታይ አመታት መመታቸውን ገልጿል።
የዲቴክ ዋና ስራ አስፈጻሚ ዲምትሮ ሳክሀሩክ በብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ቀርበው ሩሲያ በፈረንጆቹ መጋቢት 22 እና 29 በተርማል እና በውሃ ኃይል ማመንጫ ጣቢዎች ላይ መጠነሰፊ ጉዳት አድሳለች ብለዋል።
ሁለት አመት ያስቆጠረው የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት አሁንም እንደቀጠለ ነው።
ሩሲያ በቅርቡ በምስራቅ ዩክሬን ባደረገችው ጥቃት ወሳኝ የተባለችውን አቭዲቪካን ጨምሮ በርካታ መንደሮችን መቆጣጠር ችላለች።
ዩክሬን እነዚህን ቦታዎችን የለቀቀችው የምዕራባውያን ወታደራዊ እርዳታ በፍጥነት ባለመድረሱ ለመልቀቅ መገደዷን መግለጿ ይታወሳል።