ዩክሬን ወደ ጦር ግንባር የላከቻቸው አዳዲስ ወታደሮች ጥይት መተኮስ የሚለምዱት በጦር ሜዳ ላይ መሆኑ ተነገረ
የዩክሬን አዋጊዎች አዳዲስ የሚላኩ ወታደሮች መሰረታዊ ወታደራዊ ክህሎት ክፍተት ያለባቸው ናቸው ብለዋል
አንዳንድ የዩክሬን ወታደራዊ ማሰልጠኛዎች የጥይት እጥረት ስላጋጠማቸው አከላዊ ስልጠናን ብቻ ለመስጠት ተገደዋል ተብሏል
ዩክሬን ከሩስያ ጋር እያደረገችው ባለው ጦርነት ወደ ጦር ሜዳ የሚላኩ አዳዲስ ምልምሎች መሰረታዊ ወታደራዊ ስልጠናን በቅጡ ያልወሰዱ ናቸው ተብሏል፡፡
ዋሽንግተን ፖስት ያነጋገራቸው የዩክሬን ጦር መሪዎች አዲስ የሚገቡ ወታደሮች ጠብንጃ መፍታት እና መግጠም እንዲሁም መተኮስ የማይችሉ በመሆናቸው በውግያ ላይ ለማሰልጠን ተገደናል ብለዋል፡፡
ጦርነቱ ተባብሶ መቀጠሉን ተከትሎ ኬቭ ልምድ ያላቸው ወታደሮች እጥረት እንዳጋጠማት ከሰሞኑ በተለያዩ መገናኛ ብዙሀን መዘገቡ ይታወሳል፡፡
ከምዕራባዊያን የሚላኩ የጦር መሳርያዎችን አጠቃቀም ለማወቅ የሚወስደው ግዜ እንዳለ ሆኖ ፣በቅርቡ ተመልምለው ወደ ጦር ግንባር እየተላኩ ያሉ አዳዲስ ምልምሎች በአዋጊዎች ላይ ተጨማሪ ስራ መሆናቸው ነው የተሰማው፡፡
ከዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣ ጋር ቆይታ ያደረገው የ93ተኛ ሜካናይዝድ ብርጌድ አዛዥ አዳዲስ ምልምሎች በየምድባቸው ለአንድ ሳምንት ያህል በቀን 1500 ጥይት እየተኮሱ ኢላማ እና ተኩስ እንዲለማመዱ እያሰለጠንን ነው ብሏል፡፡
93ተኛው ሜካናይዝድ ብርጌድ ከባድ ውግያ በሚደርገባቸው ባክሙት እና ካርኪቭ እየተዋጋ የሚገኝ ሲሆን ምልምሎቹ መካከለኛ የውግያ መጠን ወዳለባቸው ስፍራዎች ተልከው በድጋሚ ስልጠና መውሰድ እንደሚገባቸውኑ የብርጌዱ አዛዥ ተናግሯል፡፡
የዩክሬን ወታደራዊ ማሰልጠኛዎች የጥይት እና የእጅ ቦንቦች እጥረት አጋጥሟቸዋል።በአንዳንድ ማሰልጠኛዎች ሰልጣኞች ሀያ ጥይት ብቻ ተኩሰው ወደ ጦር ሜዳ እንደሚላኩ ነው የተሰማው፡፡
በካርኪቭ እና ባክሙት ጠንከር ያለ ዘመቻ የተከፈተባት ኬቭ ያጋጠማትን የሰው ሀይል እጥረት ለመሙላት አዳዲሰ ወታደሮችን በመመልመል የሩስያን ጦር ለመመከት ጥረት እያደረገች ቢሆንም የጦር ሜዳ ውሎዎች ውጤት ግን የሁኔታዎችን መክበድ የሚያመላክቱ ናቸው፡፡
በቀጣይም ወደ ኔቶ አባል ሀገራት ወታደሮቿን ለስልጠና ልትልክ እንደምትችል ይጠበቃል።
አሜሪካን ጨምሮ ሌሎች ምዕራባዊያን ሀገራት ዩክሬን ያጋጠማትን የውግያ ልምድ ያላቸው ወታዳሮች እጥረት ለመቅረፍ ውግያዎች ላይ ውጤታማ የሆኑ ብዙ የሰው ሀይል የማይፈልጉ ከባባድ የጦር መሳርያዎችን ለመላክ እየመከሩ ይገኛሉ፡፡
ፈረንሳይ ምልምሎችን የሚያሳለጥኑ እና ለአዲስ የውግያ ዘመቻ የሚያዘጋጁ ወታደሮቿን ወደ ዩክሬን ለመላክ እቅድ ይዛለች፡፡
ሩሲያ በበኩሏ አንድም የኔቶ አባል በዚህ ጦርነት ላይ በየትኛውም መንገድ ወታደሮችን ልኮ ቢሳተፍ ቀይ መስመሩን እንደመተላለፍ እቆጥረዋለሁ ስትል ዝታለች፡፡