በዩክሬን የመፍንቅለ መንግስት ሙከራ ለማድረግ ሲያሴሩ ነበር የተባሉ ኃይሎች በቁጥጥር ስር ዋሉ
ተጠርጣሪዎቹ ፓርላማውን ለመቆጣጠር ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ አመራሮችን ለማስወገድ እቅድ ይዘው እንደነበር ተሰምቷል
የዩክሬን የብሔራዊ ደህንነት አገልግሎት ከሴራው ጀርባ የሩሲያ እጅ ሳይኖር አይቀርም ብሏል
በዩክሬን መፈንቅለ መንግስት ለማድረግ እና አመጽ ለማስነሳት ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ኃይሎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተሰምቷል፡፡
ቪቼ በሚል መጠሪያ የተሰየመው ቡድን አባላት በዩክሬን ዋና ከተማ ኪቭ ብጥብጥ እና አመጽ ለመቀስቀስ እንዲሁም ፓርላማውን ለመቆጣጠር አቅደው እንደነበር ተደርሶበታል ነው የተባለው፡፡
የዩክሬን ብሄራዊ ደህንነት አገልግሎት ባወጣው መረጃ ቡድኑ ፓርላማውን ከመቆጣጠር ባለፈ ቁልፍ ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ አመራሮችን ከኃላፊነት ለማንሳት አሲሮ እንደነበር ገልጿል፡፡
የመፈንቅለ መንግስት ሙከራውን ለማድረግ አቅደው የነበረው ባሳለፍነው አርብ በአደባባይ በተከበረው የህገ መንግስት ቀን ህዝባዊ አመጽ ካስነሱ በኋላ እሁድ እለት መፈንቅለ መንግስቱን ለማድረግ እቅድ ይዘው እንደነበር ነው የተነገረው፡፡
በስም ያልተገለጹ የዩክሬን እና የውጭ መገናኛ ብዙሀን መፈንቅለ መንግስቱን ለመዘገብ ዝግጅት ስለማማድረጋቸው እንደተደረሰበት በደህንነት ተቋሙ ሪፖርት ላይ ይፋ ተደርጓል፡፡
በተጠርጣሪዎቹ መኖሪያ ቤት ውስጥ በርካታ ተቀጣጣይ ፈንጆች ፣ የተለያየ አይነት የጦር መሳሪያዎች፣ ኮምፒውተሮች እና የመገናኛ መሳርያዎች ተይዘዋል፡፡
የመፈንቅለ መንግስቱ መሪ ነው የተባለ ግለሰብ ቁጥራቸው እስከ 2ሺ የሚጠጉ የታጠቁ ቅጥር ወታደሮችን መልምሎ የዩክሬን ፓርላማን ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ዝግጅቶችን አጠናቆ እንደነበር ነው የተነገረው፡፡
የዩክሬን ብሄራዊ ደህንነት አገልግሎት ግለሰቦቹ ከሩሲያ ጋር ግንኑነት ሊኖራቸው እንደሚችል ከፍተኛ ጥርጣሬ እንዳለው የገለጸ ሲሆን በይፋ ሩሲያን ለመወንጀል የሚያስችል ሁነኛ መረጃ ግን በእጁ ላይ እንደማይገኝ ገልጿል፡፡
በአሁኑ ወቅት ሕገ መንግስትን በሀይል ለመገልበጥ ሙከራ ክስ የቀረበባቸው ተጠርጣሪዎቹ ጥፋተኝነታቸው ከተረጋገጠ እስከ 10 አመት ጽኑ እስራት የሚጠብቃቸው ይሆናል።