በአፍሪካ የነበሩ የዩክሬን ወታደሮች በኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ሀገራቸው ተመለሱ
የዩክሬን ሰላም አስከባሪ ኃይል ሀገራቸው ከሩሲያ ጋር ጦርነት መጀመሯን ተከትሎ ወደ ኪቭ ለመመለስ ተገደዋል ተብሏል
ወታደሮቹ በተመድ ሰላም ማስከበር ተልዕኮ ስር በዲሞክራቲክ ኮንጎ ነበሩ
በአፍሪካ የነበሩ የዩክሬን ወታደሮች በኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ሀገራቸው ተመለሱ።
የመንግስታቱ ድርጅት በዲሞክራቲክ ኮንጎ ያለውን አለመረጋጋት ለመቆጣጠር ከተለያዩ ፈቃደኛ ሀገራት የተውጣጣ ሰላም አስከባሪ ጦር ማሰማራቱ ይታወሳል።
በዚህ ተልዕኮ ስራ ጦር ካዋጡ ሀገራት መካከል አንዷ አሁን ላይ ከሩሲያ ጋር ጦርነት ውስጥ ያለችው ዩክሬን ትገኝበታለች።
ሀገራቸው ከሩሲያ ጋር የገጠመችውን ጦርነት ለመመከት በሚል በዲሞክራቲክ ኮንጎ የነበሩ 250 የዩክሬን ወታደሮችም ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል።
እነዚህ ወታደሮች ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ በተመድ ዓመቻችነት ሲሆን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወታደሮቹን ካጓጓዙ አየር መንገዶች መካከል አንዱ መሆኑን ቢቢሲ ዘግቧል።
በተመድ ስር ያለው የሰላም ማስከበር ተልዕኮ በዲሞክራቲክ ኮንጎ ዜጎች ተቃውሞ እያስተናገደ ሲሆን፤ ሰላም አስከባሪ ጦሩ ዜጎችን ከአማጺያን ጥቃት አልታደገም በሚል አየተተቸ ይገኛል።
የሀገሬው ዜጎችም ሰላም አስከባሪ ጦሩ ሀገራቸውን ለቆ እንዲወጣ በሰላማዊ ሰልፍ በመጠየቅ ላይ ሲሆን ይህ ሰላም አስከባሪ ጦር ከሁለት ወራት በፊት 36 ተቃዋሚዎችን ተኩሶ ገድሏል ተብሏል።
ከዚሁ ተቃውሞ ጋር በተያያዘም በኬንሺያሳ ያለው የተመድ ሰላም ማስከበር ተልዕኮ ቃል አቀባይ የዲሞክራቲክ ኮንጎን ሉዓላዊነት የሚጋፋ አስተያየት ሰጥቷል በሚል ሀገሪቱቱን ለቆ እንዲወጣ ተደርጓል።
ተመድ በዓለም ላይ ፈቃደኛ ከሆኑ ሀገራት ጦር በማዋጣት በ12 ሀገራት ላይ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ያለው ሲሆን ለ22 ዓመት የቆየው እና ብዙ ገንዘብ ወጪ የተደረገበት ስምሪቱ በዲሞክራቲክ ኮንጎ ያለው ነው።