የዩክሬን የጦር መሳሪያ ክምችት እየተመናመነ እንደሆነ ተገለጸ
ለዩክሬን የጦር መሳሪያ ድጋፍ ካልተደረገ ሩሲያ የዩክሬንን የአየር ክልል ልትቆጣጠር ትችላለች ተብሏል
ምዕራባዊያን ደግሞ ለዩክሬን የጦር መሳሪያ መስጠት ሩሲያን የባሰ ጥቃት እንድትሰነዝር ሊያደርጋት ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸው ተገልጿል
የዩክሬን የጦር መሳሪያ ክምችት እየተመናመኑ እንደሆነ ተገለጸ፡፡
ለጥቂት ቀናት በሚል ከስምንት ወራት በፊት የተጀመረው የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ዘጠኝ ወር ሊሞላው በጣት የሚቆጠሩ ቀናት ብቻ ቀርተውታል፡፡
ይህ ጦርነት በዩክሬን ምድር ይካሄድ እንጂ ከዩክሬን እና ሩሲያ ጀርባ በርካታ ሀገራት በጦር መሳሪያ፣ ገንዘብ እና ሞራል ድጋፍ በማድረግ ላይ ናቸው፡፡
ጦርነቱ እንዲያበቃ በርካታ ጫናዎች እየተደረጉ ቢሆንም አሁንም የጦር መሳሪያዎች በይፋ ለዩክሬን እንዲሰጡ ግፊት በመደረግ ላይ ነው፡፡
መቀመጫውን ለንደን ያደረገው ሮያል ዩናይትድ ሰርቪስ ኢንስቲትዩት በዩክሬን የተለያዩ ወታደራዊ ቀጠናዎች ተጉዞ ባወጣው ሪፖርት የዩክሬን የጦር መሳሪያ ተመናምኗል ብሏል፡፡
ድርጅቱ ከዩክሬን የውጊያ ግንባር ወታደሮች፣ አዋጊዎች አና ወታደራዊ ደህንነቶችን አነጋግሮ ያወጣውን ሪፖርት ዋቢ አድርጎ ሮይተርስ እንደዘገበው ከሆነ ሩሲያ በቀጣይ የዩክሬንን ዋና ዋና ከተሞች ልትደበድብ ትችላለች፡፡
ዩክሬን ከሩሲያ ሊሰነዘርባት የሚችለውን የአየር ላይ ጥቃት መመከት የሚያስችል የጦር መሳሪያ ክምችቷ መመናመኑንም ድርጅቱ አስታውቋል፡፡
በተለይም ሩሲያ በዩክሬን የጀመረችውን ልዩ ዘመቻ እንዲመሩ የተሾሙት አዲሱ የሩሲያ ጦር አዛዥ ጀነራል ሰርጊ ሱሮቪኪ ወይም አርማጌዶን በመባል የሚታወቁት አዛዥ የዩክሬንን ዋና መሰረተ ልማት እና ከተሞችን ለመደብደብ የማያመነቱ እንደሆነም ተጠቅሷል፡፡
ሩሲያ እስካሁን ኢራን ሰራሽ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን ወደ ዩክሬን በመላክ የሀይል መሰረተ ልማቶችን ደብድባለች የተባለ ሲሆን በቀጣይ ደግሞ መካከለኛ እና ረጅም ርቀት ተጓዥ ሚሳኤሎችን ልትጠቀም እንደምትችል ተሰግቷል፡፡
ምዕራባዊያን ሀገራት ዩክሬን ከሩሲያ የሚደርስባትን ጥቃት መመከት የሚያስችላትን ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎችን ድጋፍ እንዲያደርጉ ይሄው ድርጅት አስታውቋል፡፡
ይሁንና ምዕራባዊያን ሀገራት የሩሲያን የጦር መሳሪያዎች ጥቃት ማምከን የሚያስችሉ ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎችን ቢሰጡ ፕሬዝዳንት ፑቲን ጦራቸው ተጨማሪ እርምጃዎችን እንዲወስድ ሊያዙ ይችላሉ የሚሉ ስጋቶች እንደገባቸው ዘገባው አክሏል፡፡