ኢራን ለሩስያ የምትሰጠው የባላስቲክ ሚሳኤሎች ቁጥር በአስጊ ደረጃ እየጨመረ እንደሚገኝ አሜሪካ አስታወቀች
ኢራን በበኩሏ በምዕራባውያን የሚቀርበው ክስ ሀሰተኛ ነው በሚል ታጣጥላለች
ባሳለፍነው ወር በሳተላይት የሚመሩ የኢራን ባላስቲክ ሚሳኤሎችን አጠቃቀም ለመሰልጠን የሩስያ ወታደሮች ወደ ቴሄራን ማቅናታቸው ተዘግቧል
ኢራን ለሩስያ የምትሰጣቸው የባላስቲክ ሚሳኤሎች መጠን እየጨመረ እንደሚገኝ አሜሪካ ገለጸች፡፡
ሀገሪቱ በአስጊ ሁኔታ እየጨመረ ነው ያለችው የመካከለኛ ርቅት ተምዘግዛጊ ሚሳኤሎች በዩክሬን ጦርነት ላይ ጥቅም ላይ እየዋሉ እንደሚገኝ ነው ያስታወቀችው፡፡
በቅርብ ሳምንታት ሁለቱ ሀገራት የሚያደርጉት የጦር መሳርያ ልውውጥ እንቅስቃሴ በአይነት እና መጠን ከፍ ያለ መሆኑን አሜሪካ ገልጻለች፡፡
ባሳለፍነው ወር ፋታ-360 የተባሉትን ሳተላይት መር የመካከለኛ ርቀት ተምዘግዛጊ ሚሳኤሎችን አጠቃቀም ለመሰልጠን በደርዘን የሚቆጠሩ የሩስያ ጦር አባላት ወደ ኢራን ማቅናታቸው ተዘግቦ እንደነበር ይታወሳል፡፡
የነጩ ቤተ መንግስት ብሔራዊ ደህንነት ካውንስል ቃል አቀባይ ሾን ሳቬት ሞስኮ በኬቭ ላይ ጥቃት ከከፈተች አንስቶ በሁለቱ ሀገራት ያለው የመከላከያ ትብበር በማደግ ላይ እንደሚገኝ በቅርበት እየተከታተልን ነው ብለዋል፡፡
ቴሄራን ለሞስኮ የምታደርገው ማንኛውም የጦር መሳርያ የየክሬኑን ጦርነት በማባበስ የሚኖረው ሚና ከፍተኛ እንደሆነ የተናገሩት ቃል አቀባዩ ኢራን ለዚህ ተግባሯ የማዕቀብ እርምጃ ሊወሰድባት እንደሚችል አስጠንቅቀዋል፡፡
በተመድ የኢራን አምባሳደር በበኩላቸው በዩክሬን ጉዳይ የሀገራቸው አቋም እንዳልተለወጠ ተናግረው፤ እርሱም ለሁለቱም ሀገራት የሚደረጉ የጦር መሳርያ ድጋፎች የንጹሀንን ሞት ከመጨመር እና ውግያውን ከማፋፋም እንዲሁም የሰላም ድርድሮች እንዳይካሄዱ እንቅፋት ከመሆን የዘለለ ሚና የለውም ሲሉ አስታውሰዋል፡፡
ሩሲያ በዩክሬን ላይ በፈጸመችው ጥቃት 50 ሰዎች ተገደሉ
አምባሳደሩ ምዕራባውያን ኢራንን ለሩስያ ጦር መሳርያ ድጋፍ በማድረግ ያልተረጋገጠ ክስ ከሚያቀርቡ ይልቅ እነርሱ በይፋ ለዩክሬን በገፍ የሚያደርጉትን የጦር መሳርያ ድጋፍ አቁመው ጦርነቱ በድርድር በሚጠናቀቅበት ሁኔታ ላይ ሰላማዊ መፍትሄን ቢያፈላልጉ የተሻለ ነው ብለዋል፡፡
ከአሜሪካ በተቃራኒ የሚገኙት ተሄራን እና ሞስኮ ከዚህ ቀደም የነበራቸውን የስትራቴጂካዊ አጋርነት ስምምነት በአዲስ ለመተካት እየተደራደሩ በሚገኙበት ወቅት የቀድሞ የኢራን ፕሬዝዳነት በድንገተኛ አደጋ ህይወታቸው በማለፉ ስምምነቱ እንዲቆይ ተደርጓል፡፡
ይህ ስምመነት ሀገራቱ በነዳጅ ሽያጭ ፣ በኢኮኖሚ እና በወታደራዊ ጉዳዮች ላይ አጋርነታቸውን የሚያጠናክር ነው