ፕሬዝዳንቱ አዲስ ሹም ሽር ባደረጉበት ምሽት ሩሲያ ዩክሬንን በሚሳዔል ስትደበድብ አድራለች
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሊድምር ዘለንስኪ ረዳቶቻቸውን ከስራ ማባረራቸው ተገለጸ።
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሊድሚር ዘለንስኪ የረዥም ጊዜ ረዳታቸው የነበሩትን ሴርሂይ ሸፊርን ጨምሮ በርካታ አማካሪዎችን በትናትናው ዕለት ማሰናበታቸው ታውቋል።
ዘለንስኪ ከኃፊነት ካባረሯቸው ባለስልጣናት መካከል ከፈረንጆቹ 2019 ጀምሮ የፕሬዝዳንቱ ከፍተኛ ረዳት በመሆን ሲያገለግሉ የቆዩት ሴርሂይ ሸፊር አንዱ ናቸው።
የዩክሬን ፕሬዝዳንት በተጨማሪም ሶስት አማካሪዎችን እና ሁለት የፕሬዚዳንት ተወካዮች ከስራ ማሰናበታቸው ነው የተገለጸው።
ፕሬዝዳንት ቮሊድሚር ዘለንስኪ ካሳለፍነጫው ወራት ወዲህ ከፍተኛ የሆነ ሹም ሽር እያደረጉ ሲሆን፤ ምክንያቱ ግን እስካሁን በግልጽ እንዳላታወቀም ነው የተነገረው።
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ባሳለፍነው ሳምንት ማክሰኞ የብሔራዊ ደኅንነት እና የመከላከያ ምክር ቤት ፀሐፊ ሆነው ያገለገሉት ኦሌክሲይ ዳኒሎቭ እና የጦር ኃይሎች መሪ ቫለሪ ዛሉዥኒ ከኃላፊነታቸው ማሰናበታቸውም ይታወሳል።
በተያያዘ ዜና ፕሬዝዳንት ቮሊድሚር ዘለንስኪ አዲስ ሹም ሽር ባደረጉበት ምሽት ሩሲያ ዩክሬንን በሚሳዔል እና በድሮን ስትደበድብ አድራለች።
ትናንት ምሽት ብቻ ሩሲያ በ12 የሼድድ ድሮኖች እና አራት ሚሳዔሎች በዩክሬን ላይ ጥቃት የሰነዘረች ሲሆን፤ ከድሮኖቹ መካከል 9 ተመትተው መውደቃቸውን ዩክሬን ጦር አስታውቋል።
ሩሲያ በ24 ሰዓታት ውስጥ ብቻ በዩክሬን ላይ 38 የሚሳዔል ጥቃቶች፣ 75 የአየር ድብደባዎች እና 98 የሮኬት ጥቃቶችን መሰንዘሯንም የዩክሬን ጦር አስታውቋል።
ሩሲያ በዶኔስክ ክልል ባደረሰችው ጥቃትም 2 ሰዎች መሞታው እና አንድ ሰው ደግሞ መቁሰሉም ተነግሯል።