የዩክሬን አርሶ አደሮች የጥይት መከላከያ ለብሰው እርሻቸውን ቀጥለዋል
የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ 70 ቀናት ሞልቶታል

የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት የስንዴ ልማት ስራዎች የሚከናወኑበት ወቅት ላይ መሆኑ ስንዴ አምራቾችን እየፈተነ ነው
በደቡባዊ ክልል የሚኖሩ የዩክሬን አርሶ አደሮች ማሳቸውን ለማረስ የጥይት መከላከያ እየለበሱ መሆኑ ታውቋል።
ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ ቃልኪዳን ጦር ወይም ኔቶን እቀላቀላለሁ ማለቷን ተከትሎ ከሩሲያ ጋር ወደ ጦርነት ካመራች 70ኛው ቀን ላይ ይገኛል።
በዚህ ጦርነት ምክንያት ከ6 ሚሊየን በላይ ዩክሬናዊያን ወደ ጎረቤት ሀገራት የተሰደዱ ሲሆን ከተሞች፣ መኖሪያ መንደሮች እና መሰረተ ልማቶች በመውደም ላይ ይገኛሉ።
የሁለቱ ሀገራት ጦርነት በተለይም የስንዴ ልማት ስራዎች የሚከናወኑበት ወቅት ላይ መሆኑ ስንዴ አምራች ዩክሬናዊያን አርሶ አደሮችን በመፈተን ላይ ነው።
ይህ የስንዴ አዝመራ ወቅት እንዳያልፋቸው የሰጉ ዩክሬናዊያን ገበሬዎች የጥይት መከላከያ ጃኬት እና ሄልሜት አድርገው ስንዴ ማልማታቸውን ቀጥለዋል ሲል ሮይተርስ ዘግቧል።
አርሶ አደሮቹ ከሩሲያ የሚተኮሱ ሚሳኤሎች እና ከባድ መሳሪያዎች እንዳያገኟቸው የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም ላይ ናቸው።
የጦርነቱ ተኩስ ልውውጥ ሲበረታ መኖሪያ ቤታቸው ውስጥ በመደበቅ ተኩስ ጋብ ሲል ደግሞ ወደ ማሳቸው ጥይት የማይበሳቸው ሄልሜቶችን እያደረጉ በመሄድ ስራቸውን ቀጥለዋልም ተብሏል።
በተለይም የሩሲያ ሮኬት ጥቃቶች በጣም አስፈሪ ናቸው የሚሉት እነዚህ ዩክሬናዊያን አርሶ አደሮች ጦርነቱ አጠቃላይ ህይወታቸውን እንደቀየረው እና ወቅቱ እንዳያልፋቸውም ትግል ላይ መሆናቸውን አክለዋል።
በዩክሬን ልዩ ዘመቻ በሚል ይፋዊ ጦርነት የጀመረችው ሩሲያ አሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረትን ጨምሮ በተለያዩ ሀገራት ከ6 ሺህ በላይ ማዕቀቦች ተጥሎባታል።
ምዕራባዊያን በተለይም የሩሲያ ነዳጅ በዓለም እንዳይሸጥ ማዕቀቦች የተጣሉባት ሲሆን፤ ሩሲያ በበኩሏ ወዳጅ አይደሉም ያለቻቸው ሀገራት ነዳጅ በሩብል እንዲገዙ ውሳኔ አስተላልፋለች።