የፀጥታው ምክር ቤት በሶማሊያ ላይ የተጣለውን የጦር መሳሪያ ማእቀብ ለተጨማሪ አንድ አመት አራዘመ
ውሳኔውን ሩስያ፣ ቻይና፣ ጋቦን እና ጋና ተቃውመውታል
የእገዳው መራዘም ሽብርተኝነትን ለመዋጋት የሚደረገውን ጥረት ያደናቅፋል የሚል ስጋት ፈጥሯል
የመንግስታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ሶማሊያ ላይ የተጣለውን የጦር መሳሪያ እቀባ ለተጨማሪ አንድ አመት አራዝሞታል።
የእገዳ ውሳኔውን ከሩስያ እና ቻይና ውጭ የፀጥታው ምክር ቤት ሁሉም አባላት ተቃውመውታል።የአፍሪካ የወቅቱ የፀጥታው ምክር ቤት ወኪሎች ጋቦን እና ጋናም ተቃውሟቸውን ገልጸዋል ተብሏል፡፡
የሶማሊያ መንግስት በበኩሉ አዲሱን ውሳኔ አስደንጋጭ ነው ብሎታል።
በመንግስታቱ ድርጅት የሶማሊያ ቋሚ መልዕክተኛው አምባሳደር አቡካር ባሊ፥ አስነዋሪ ያሉት ውሳኔ ሽብርተኛውን አልሸባብ ለመዋጋት የሚደረገውን ጥረት የሚያደናቅፍ መሆኑን ተናግረዋል።
የፀጥታው ምክር ቤት በሶማሊያ ላይ የጣለው የጦር መሳሪያ ግዥ ክልከላ በየትኛውም ሀገር ከተላለፈው እቀባ ረጅሙ ነው።
ሶማሊያ በፈረንጆቹ 1992 ተቀስቅሶ የማዕከላዊ መንግስቱን ካፈረሰው የእርስ በርስ ጦርነት በኋላ የተጣለው እቀባ ሰላሳኛ አመቱን ይዟል።
ባለፉት ስድስት ወራት አዲሱ የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ ማህሙድ ይህን ውሳኔ ለማስነሳት ሰፊ የዲፕሎማሲያዊ ዘመቻን ሲያደርጉ ቆይተዋል።የአፍሪካ ህብረትም ይህንኑ ጥረታቸውን እንዲያግዝ ሲወተውቱ እንደነበር የሚታወስ ነው።
ፕሬዚዳንቱ በሽብርተኞች ላይ ጦርነት አውጀው የሶማሊያ ጦርና የአልሸባብ ታጣቂዎች ከባድ ውጊያ ውስጥ በገቡበት በአሁኑ ወቅት የፀጥታው ምክር ቤት ያሳለፈው ውሳኔ ሞቃዲሾን አስቆጥቷል።
እቀባው የሶማሊያ መንግስትን እግር ተወርች ያስራል የሚሉ ቅሬታዎችም እየተደመጡ ነው።በቀጠናው የሽብር ተግባሩን እያሰፋ የሄደውን አልሸባብ ይበልጥ እንዳያጠናክረውም ተሰግቷል።