አሜሪካ ከመጪው ወር ጀምሮ በመላው ኢትዮጵያ የምግብ እርዳታ ትጀምራለች
የአሜሪካ ዓለም አቀፍ ልማት ተራድኦ ድርጅት (ዩኤስኤአይዲ) የምግብ እርዳታ ከተቸገሩ ሰዎች ተነጥቋል በሚል ድጋፉን ማቋረጡ ይታወሳል
ዩኤስኤአይዲ የእርዳታ ስርጭቱን ለመቆጣጠር ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን ገልጿል
አሜሪካ በኢትዮጵያ አቋርጣው የነበረውን የምግብ እርዳታ ከመጪው ወር ጀምሮ ዳግም ልትጀምር መሆኑን አስታውቃለች።
የአሜሪካ መንግስት የዓለም አቀፍ ልማት ተራድኦ ድርጅት (ዩኤስኤአይዲ) በሰኔ ወር ነበር የምግብ እርዳታ ከተቸገሩ ወገኖች ላይ ተሰርቋል በሚል እርዳታውን ያቋረጠው።
በለጋሾች የተገዛ የምግብ እርዳታ ለገበያ መቅረቡና ወደ ውጪ አገራት ጭምር መላኩን የጠቀሰው የተራድኦ ድርጅቱ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር የእርዳታ ስርጭቱን በተመለከተ ተከታታይ ውይይት ማድረጉን ገልጿል።
በዚህም ባለፈው ወር በሀገሪቱ ለሚገኙ ስደተኞች የምግብ እርዳታ ማቅረብ የጀመረ ሲሆን፥ ከመጪው ወር ጀምሮ ደግሞ በመላው ኢትዮጵያ ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች እርዳታ ማቅረብ እንደሚጀምር ማሳወቁን ሬውተርስ ዘግቧል።
ኢትዮጵያ የምግብ ድጋፍ ስርጭት ስርአቷን በመሰረታዊነት የሚያስተካክል ስራ መከወኗንና ለጋሽ ድርጅቶች እርዳታው ለተገቢው አካል መድረሱን እንዲከታተሉ መስማማቷን ድርጅቱ አስታውቋል።
ለጋሽ ድርጅቶች በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል ጫና ሳይደረግባቸው እርዳታ ለሚገባው ወገን መድረሱን ማረጋገጥ እንዲችሉ መፍቀዷንም ነው የዩኤስኤይድ መግለጫ ያመላከተው።
በ30 ዓመታት ታይቶ አይታወቅም በተባለ ድርቅና በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት በኢትዮጵያ 20 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች የምግብ እርዳታ ይሻሉ።
ሀገሪቱ ከ850 ሺህ በላይ ስደተኞችን በማስተናገድ ላይ ስትሆን ፥ ከ35 ሺህ በላይ ሱዳናውያን ጦርነትን ሽሽት ወደ ኢትዮጵያ ገብተዋል።
የአለም ምግብ ፕሮግራምና የአሜሪካ ዓለም አቀፍ ልማት ተራድኦ ድርጅት በእርዳታ ስርቆት ምክንያት ድጋፍ አቋርጠው መቆየታቸውም ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱ ሲነገር ቆይቷል።
የአሜሪካ መንግሥት በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚሊዮኖች ከፍተኛውን ሰብአዊ እርዳታ በማቅረብ ከሌሎች አገራት እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች መካከል ዋነኛው መሆኑ ይታወቃል።
ዩኤስኤአይዲ በ2021 ብቻ ለኢትዮጵያ 18 ቢሊየን ብር መመደቡን ማሳወቁ የሚታወስ ነው።