ተመድ የጋዳፊን ልጅ ጉዳይ በሚመለከተው “ፍርድ ቤት ላይ የደረሰው ጥቃት አሳስቦኛል” አለ
ሰኞ በተጠናቀቀው የሊቢያ ምርጫ የዕጩዎች ምዝገባ 60 ሰዎች ሀገሪቱን በፕሬዝዳንት ለመምራት ተመዝግበዋል
የሰይፍ አል-ኢስላም ጠበቃ ካህሊ አል-ዛኢዲ "ድርጊቱ ለምርጫ ሂደቱ እንቅፋት ነው" ብለውታል
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቀድሞ የሊቢያ መሪ ልጅ ሳኢፍ አል ኢስላም ጋዳፊ ይግባኝ ባቀረበበት ፍርድ ቤት ላይ የተፈጸመው ጥቃት አሳስቦኛል አለ።
የቀድሞ የሊቢያ መሪ የሙአማር ጋዳፊ ልጅ ሰይፍ ሳኢፍ አል ኢስላም ጋዳፊ ከሊቢያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ዕጩነታቸው መሰረዛቸውን የሀገሪቱ ምርጫ ኮሚሽን በሃሙስ እለት መግለጹ ይታወሳል።
የቀድሞው መሪ ልጅ ከዕጩነት የተሰረዙበት ምክንያት “በሕግ የሚያስጠቃቸው ጉዳይ ስላለ” ነው ብሎም ነበር ኮሚሽኑ።
የሳኢፍ አል ኢስላም አባት ጋዳፊ የሰሜን አፍሪካዊቷ ሀገር ሊቢያን በሚያስተዳደሩበት ወቅት በተፈጸሙ በዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት በጦር ወንጀል እና በነፍስ ግድያ የሚፈለጉ ሰው ነበሩ።
በዚህም የተነሳ የጋዳፊ ልጅ ለፕሬዚዳንትነት እንደሚወዳደሩ ከተሰማ በኋላ ውዝግብ አስነስቷል።
የ ሳኢፍ አል ኢስላም ጠበቃ ካህሊ አል-ዛኢዲ ሴባህ ከተማ በሚገኘው ፍርድ ቤት የደንበኛውን አቤቱታ ለፍርድ ቤቱ እንዳያቀርብ የታጠቁ ሰዎች እንደከለከሉት ተናግሯል።
ሴባህ ከተማ ሊቢያን ለመቆጣጠር ነፍጥ ካነሱት አንዱ በሆኑት ጄነራል ኻሊፍ ሃፍጣር ቁጥጥር ሥር የምትገኝ ናት።
ካሊድ አል-ዛይዲ በሊቢያ መገናኛ ብዙሃን ላይ በቀረበው ቪዲዮ ባስተላለፉት መልእክት "ድርጊቱ ለምርጫ ሂደቱ እንቅፋት ነው" ሲሉ ተናግረዋል።
በፈረንጆቹ ታህሳስ 24 ቀን 2021 ይካሄዳል ተብሎ ከሚጠበቀው ምርጫ በርካታ ዕጩዎች መሰረዛቸው ወደ ዴሞክራሲ ትጓዛለች ተብላ የምትጠበቀው ሊቢያን ወደሌላ ቀውስ እንዳይወስዳት ያሰጋል ተብሏል።
በተመሳሳይ በአሜሪካ ፍርድ ቤቶች የወንጀል ክስ የቀረበባቸው ዝነኛው ኻሊፍ ሃፍጣር ለዚሁ ምርጫ ለመወዳደር መዘጋጃታቸው በሀገሪቱ ውስጥ ውዥንብር መፍጠሩ አልቀረም።
የሀገሪቱ ምርጫ ኮሚሽኑ ኻሊፍ ሃፍጣርን ከፕሬዝዳንታዊው ምርጫ ውጪ ያድርጋቸው አይድርጋቸው የታወቀ ነገር የለም ተብሏል።
የሊቢያ ወታደራዊ ዐቃቤ ሕግ የጋዳፊ ልጅ እና የሃፍታር በቀረበባቸው ክስ ላይ ተገቢ መልስ እስኪያቀርቡ ድረስ የምርጫ ኮሚሽኑን በዕጩነት ለማሳተፍ የሚያደርገውን ሂደት እንዲያቆም ጠይቀው ነበር።
ሰኞ በተጠናቀቀው የዕጩዎች ምዝገባ 60 ሰዎች ሊቢያን በፕሬዝዳንት ለመምራት የተመዘገቡ ሲሆን የ46 ዓመቷ የሴቶች መብት ተሟጋች ሊላ ቤን ካሊፋ ብቸኛዋ ሴት ተወዳዳሪ ናቸው።