መቀሌ ለማረፍ ተችግራ ተመለሰች ስለተባለችው የተመድ አውሮፕላን ጉዳይ
የተመድን የሰብአዊ እርዳታ የጫነ አውሮፕላን በአየር ድብደባው ምክንያት መቀሌ ማረፍ አልቻለም ተብሏል
በራሳቸው ምክንያት ካልሆነ በስተቀር ሁለቱ በረራዎች አይገናኙም- መንግስት
ሮይተርስ ሁለት የሰብአዊ እርዳታ ሰራተኞችን ጠቅሶ እንደዘገበው፤ የተመድን የሰብአዊ እርዳታ የጫነ አውሮፕላን መንግስት በትግራይ ባካሄደው የአየር ድብድባ ምክንያት መቀሌ ማረፍ አልቻለም ብሏል።
ሮይተርስ በዚህ ጉዳይ ሁለት ሰማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ሰዎችን ማናገሩን ጠቅሷል።
- የህወሓትን የዉጊያ ግንኙነት ኔት ወርክ ዒላማ ያደረገ የአየር ድብደባ መፈጸሙን መንግስት አስታወቀ
- በመቀሌ ተፈጸመ ስለተባለው የአየር ድብደባ መንግስት ምን ምላሽ አለው?
ጉዳዩን በተመለከተ አል ዐይን ኒውስ ከመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ጋር የሥልክ ቆይታ አድርጓል።
ዶ/ር ለገሰ እንደገለጹት በራሳቸው ምክንያት ካሆነ በስተቀር የአየር ድብደባው እና የሰብአዊ እርዳታ ጫኝ አውሮፕላን እንቅስቃሴ አይገናኝም ብለዋል።
“አንደኛ ሰዓቱ የተለያየ ነው” ያሉት የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ዶ/ር ለገሰ፤ “መዳረሻዎችም የተለያዩ ናቸው” ሲሉም ተናግረዋል።
መንግስት በአስቸኳይ ጊዜ መረጃ ማጣሪያ ዛሬ ገጹ ባወጣው መግለጫ “ሌላው የአሸባሪው የህወሓት ማሰልጠኛ ማዕከል ዛሬ የአየር ጥቃት ዒላማ ሆኗል” ብሏል።
ማዕከሉ “ለአሸባሪው ቡድን ወታደራዊ ሥልጠና ከመዋሉ በፊት የኢፌዴሪ መከላከያ ማሠልጠኛ ማዕከል” እንደነበርም ነው በማጣሪያ ገጹ የሰፈረው፡፡
አሁኑ ላይ ግን “አሸባሪው ቡድን በዚህ ተቋም ውስጥ ወታደራዊ ስልጠና የሚሠጥበት፤ የዉጊያ ግንኙነት ኔት ወርክ ያለበት” ነውም ብሏል።
ከሰሞኑ በመቀሌ የአየር ድብደባዎች እየፈጸመ መኆኑን መንግስት ልክ እንደዛሬው ሁሉ በይፋዊ የመረጃ ማጣሪያ ገጹ በኩል አስታውቋል።