ዛሬ የህወሓትን የጦር መሳሪያ ማምረቻዎች በአየር መደብደቡን መንግስት አስታወቀ
ከሰሞኑ በመቀሌ የአየር ድብደባዎች ተፈጽመዋል በሚል ሲነገር እንደነበር ይታወሳል
ሆኖም ድብደባው በየትኛው አካባቢ እንደተፈጸመ አልተገለጸም
መከላከያ ሠራዊት በህወሀት ጦር መሳሪያ ማምረቻዎች ላይ የአየር ድብደባ መፈጸሙ ተገለጸ፡፡
የመንግስት የአስቸኳይ ጊዜ የመረጃ ማጣሪያ የአየር ድብደባውን በተመለከተ መግለጫ አውጥቷል፡፡
ሰራዊቱ የፈጸማቸውን የአየር ድብደባዎች በተመለከተ የተዛባ ግንዛቤ መኖሩን የጠቆመው መግለጫው ጥቃቶቹ በተቃራኒው የህወሓት የጦር መሣሪያ ማምረቻ እና የጦር ትጥቅ ጥገና ጣቢያዎችን ብቻ ዒላማ ማድረጋቸውን አስታውቋል።
በመቀሌ ተፈጸመ ስለተባለው የአየር ድብደባ መንግስት ምን ምላሽ አለው?
የአየር ላይ ድብደባው የሽብር ድርጅቱ ከባድ የጦር መሣሪያዎችን እና ሌሎች ሕገወጥ የጦር መሣሪያዎችን ለመሸሸግ የሚጠቀምባቸውን እና ወደ ወታደራዊ መገልገያነት የቀየራቸውን የተወሰኑ ቦታዎች ከጥቅም ውጭ ለማድረግ በማሰብ መፈጸሙንም ገልጿል።
ሆኖም ግን የአስቸኳይ ጊዜ የመረጃ ማጣሪያው ድብደባው በየትኛው አካባቢ እንደተፈጸመ አልገለጸም፡፡
ከትናንት በስቲያ ሰኞ ጥቅምት 8 ቀን 2014 ዓ/ም በመቀሌ የአየር ድብደባዎች መፈጸማቸውን የሚያመለክቱ መረጃዎች በተለያዩ የመገናኛ መንገዶች ሲሰራጩ ነበረ፡፡
በጥቃቱ በገበያ ስፍራ ላይ የተፈጸመ እንደሆነ ሲገልጹ የነበሩ የህወሓት አመራሮች ንጹሃን መገደላቸውን በመጠቆም በተለያዩ የማህበረሰብ ትስስር ገጾች ሲጽፉም ነበረ፡፡
ሆኖም ድብደባውን በተመለከተ ከአል ዐይን አማርኛ ጋር የስልክ ቆይታ ያደረጉት የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) መንግስት የራሱን ከተማ በምን ምክንያት ይበድባል ሲሉ መልሰዋል፡፡
ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ መንግስት የራሱ ዜጎች የሚኖሩበትን ከተማ እንዲሁም የራሱን ዜጎች ሊያጠቃ የሚችልበት ምንም ምክንያት እንደማይኖርም ነው የገለጹት፡፡
ነገር ግን መንግስት ለሀገር ስጋት ችግር ይፈጥራል ያለውን ጉዳይ በየትኛውም ሰዓት እና በማንኛውም ሁኔታ ንጹሃን ዜጎችን በጠበቀ መልኩ ሊመታ እንደሚችል አልሸሸጉም፡፡ ለዚህ ማንንም ማስፈቀድ እንደማይጠበቅበት ተናግረዋል።