የህወሓትን የዉጊያ ግንኙነት ኔት ወርክ ዒላማ ያደረገ የአየር ድብደባ መፈጸሙን መንግስት አስታወቀ
የአየር ድብደባው ከሰኞ ጀምሮ የቀጠለ ሲሆን የዛሬው ለ4ኛ ጊዜ መሆኑ ይታወቃል
የአየር ድብደባው በቀድሞው የኢፌዴሪ መከላከያ ማሠልጠኛ ማዕከል ላይ የተፈጸመ ነው ተብሏል
የኢትዮጵያ አየር ሀይል ለአራተኛ ጊዜ በህወሓት ወታደራዊ ማዘዣ ጣቢያ ላይ የአየር ድብደባ መፈጸሙ ተገለጸ፡፡
መንግስት በአስቸኳይ ጊዜ መረጃ ማጣሪያ ገጹ ባወጣው መግለጫ “ሌላው የአሸባሪው የህወሓት ማሰልጠኛ ማዕከል ዛሬ የአየር ጥቃት ዒላማ ሆኗል” ብሏል፡፡
ማዕከሉ “ለአሸባሪው ቡድን ወታደራዊ ሥልጠና ከመዋሉ በፊት የኢፌዴሪ መከላከያ ማሠልጠኛ ማዕከል” እንደነበርም ነው በማጣሪያ ገጹ የሰፈረው፡፡
አሁኑ ላይ ግን “አሸባሪው ቡድን በዚህ ተቋም ውስጥ ወታደራዊ ስልጠና የሚሠጥበት፤ የዉጊያ ግንኙነት ኔት ወርክ ያለበት” ነውም ብሏል።
ከሰሞኑ በመቀሌ የአየር ድብደባዎች እየፈጸመ መኆኑን መንግስት ልክ እንደዛሬው ሁሉ በይፋዊ የመረጃ ማጣሪያ ገጹ በኩል አስታውቋል፡፡
በመቀሌ ተፈጸመ ስለተባለው የአየር ድብደባ መንግስት ምን ምላሽ አለው?
የአየር ላይ ድብደባው የህወሓት ከባድ የጦር መሣሪያዎችን እና ሌሎች ሕገወጥ የጦር መሣሪያዎችን ለመሸሸግ የሚጠቀምባቸውን እና ወደ ወታደራዊ መገልገያነት የቀየራቸውን የተወሰኑ ቦታዎች ከጥቅም ውጭ ለማድረግ በማሰብ የሚፈጸም ነው እንደ መንግስት ገለጻ።
የኢትዮጵያ አየር ሀይል በያዝነው ሳምንት ከሰኞ ጥቅምት 8 ቀን 2014 ዓ/ም ጀምሮ በመቀሌ እና አካባቢው የአየር ድብደባዎች መፈጸማቸውን መንግስት አሳውቋል፡፡
የአየር ላይ ጥቃቱ በገበያ ስፍራ ላይ የተፈጸመ እንደሆነ ሲገልጹ የነበሩ የህወሓት አመራሮች ንጹሃን መገደላቸውን በመጠቆም በተለያዩ የማህበረሰብ ትስስር ገጾች ሲጽፉም ነበር፡፡
ነገር ግን መንግስት ለሀገር ስጋት ችግር ይፈጥራል ያለውን ጉዳይ በየትኛውም ሰዓት እና በማንኛውም ሁኔታ ንጹሃን ዜጎችን በጠበቀ መልኩ ሊመታ እንደሚችል አስታውቋል፡፡